በጥቃቱ በእስራኤል በኩል እስካሁን 700 ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል
እስራኤል ለሀማስ ምላሽ ለመስጠት በጀመረችው ጥቃት ክብረ-ወሰን የተሻገረ ነው የተባለ 300 ሽህ ተጠባባቂ ኃይሎችን መመልመሏ ተነግሯል።
የእስራኤል ጦር ከቅዳሜ ጀምሮ በአስቸኳይ የተጠሩ 300 ሽህ ተጠባባቂ ኃይል አለ ብሏል።
ጦሩ ከዚህ ቀደም ይህን ያህል ወታደር በአጭር ጊዜ መልምሎ እንደማያውቅም ገልጿል።
በሀማስ ቅዳሜ ላይ በድንገት የተጠቃችው እስራኤል በጋዛ የአየር ድብደባዋን ቀጥላለች።
የእስራኤል የምድር ጦሯ የሀማስ ታጣቂዎች የተያዙ የድንበር መንደሮችንና ከተማዎች ለመቆጣጠር እየተፋለመ ነው ተብሏል።
የሀገሪቱ ጦር ቃል አቀባይ በታጣቂዎች የተያዙ አካባቢዎች እየተመለሱ ነው ያሉ ሲሆን፤ ሆኖም ታጣቂዎች አሁንም እየተዋጉ ነው ብለዋል።
የእስራኤል የወታደራዊ ሹማምንት በሀማስ ላይ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ድንበሩን መቆጣጠር ቅድሚያ እንደሚሰጠው ገልጸዋል።
ቃል አቀባዩ በጥቃቱ በእስራኤል በኩል 73 የጸጥታ መኮንኖችን ጨምሮ እስካሁን 700 ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጧል።
የእስራኤል ጦር ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሀማስ ታጣቂዎችን መግደሉንም ተናግረዋል።