ፓርላማው ህዳር 1 ምርጫ እንዲካሄድ ወስኗል
የእስራኤል ተወካዮች ምክር ቤት (ክኔሴት) ተበተነ፡፡
ፓርላማው ዛሬ ሃሙስ ራሱ በሰጠው ድምጽ ነው መበተኑን የወሰነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከዓመት በፊት የኒታኒያሁን መንግስት አሸንፈው ስልጣን የተቆጣጠሩት 8 ተቃዋሚ ፓርቲዎች በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ አለመስማማታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
በተለይም የዌስት ባንክ ሰፈራ እና የከተማ ባቡር (ሜትሮ) ግንባታ ፖሊሲ ጉዳይ እንዳለያያቸው ነው የሚነገረው፡፡ በዚህም ፓርላማውን በትነው በመጪው ህዳር 1 (በፈረንጆቹ) ምርጫ ለማካሄድ ተስማምተዋል፡፡
ምርጫው በአራት ዓመታት ውስጥ ለ5ኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው፡፡
የፓርላማውን መበተን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዬይር ላፒድ ባላደራ ጠቅላይ ሚኒትር ሆነዋል፡፡ ምርጫ እስከሚደረግበት ጊዜ ድረስም እስራኤልን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ይመራሉ፡፡
ላፒድ ናፍታሊ ቤኔትን በመተካት ነው ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት፡፡ የጥምር መንግስቱን ሲመሰርቱ ተተካክተው ሃገሪቱን የመምራት ስምምነት ነበራቸው፡፡
ከጥቂት ሰዓታት በፊት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ቤኔት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሃገራቸውን የሚያገለግሉም ይሆናል፡፡ ቤኔት በቀጣዩ ምርጫ ዬሽ አቲድ የተባለውን ፓርቲያቸውን ወክለው ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደማይወዳደሩ አስታውቀዋል፡፡
የፓርላማውን መበተን እና ለ5ኛ ጊዜ ምርጫ እንዲካሄድ መገደዱን የተቹት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድሮውን በሃሳብም ሆነ በፖሊሲ የማይቀራረቡ ፓርቲዎች መጣመራቸውን ተናግረዋል፡፡
አሁንም የላፒድ ውጤታማነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡ በእስራኤል ታሪክ ያልተሳካለት የፋይናንስ ሚኒስትር ሲሉም ወርፈዋቸዋል፡፡
የቀድሞው ዜና አንባቢ እና ጋዜጠኛ ላፒድ በኔታንያሁ የስልጣን ዘመን በፋይናንስ ሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡