በእስራኤል የአየር ጥቃት 40 ሊባኖሳውያን ተገደሉ፤ 53 ሰዎች ቆስለዋል
የእስራኤል ጄቶች በቤሩት አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያም ጥቃት መፈጸማቸው ተገልጿል
የሄዝቦላህ አዲሱ መሪ “እስራኤል ወረራዋን ካቆመች ለተኩስ አቁም ድርድር ዝግጁ ነን” ብለዋል
እስራኤል በምስራቃዊ ሊባኖስ በፈጸመችው የአየር ጥቃት በጥቂቱ የ40 ሰዎች ህይወት ማለፉን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በባካ እና ባልቤክ ግዛቶች በተፈጸሙት ጥቃቶች ከ53 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውንም ነው የገለጸው።
የአየር ጥቃቶቹ በባልቤክ ከተማ በሚገኘው ”ማንሺያ ህንጻ” ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሳቸውን የሊባኖስ የባህል ሚኒስትር ሞሀመድ ሞርታዳ ተናግረዋል።
ጥንታዊው ህንጻ በኦቶማኖች ዘመን የተገነባና በአለም ቅርስነት በተመዘገቡት የሮማን ቤተመንግስቶች አጠገብ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በ19ኛው ክፍለዘመን የተገነባው “ፓልሜራ ሆቴል”ም በእስራኤል የአየር ጥቃት ጉዳት እንደደረሰበት ዘግቧል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ ጄቶቹ ጥቃቱን ያደረሱት በባልቤክ አካባቢ በሚንቀሳቀሱ የሄዝቦላህ ታጣቂዎች ላይ መሆኑንና በጥብቅ የደህንነት መረጃዎች ተመርኩዘው ጥቃቱን ማድረሳቸውን ገልጿል።
ጦሩ ዛሬ ማለዳም በቤሩት አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ በሚገኝ የሄዝቦላህ ይዞታ ላይ ጥቃት ማድረሱን አስታውቋል።
በዚህም የሄዝቦላህ ማዘዣ ጣቢያዎች፣ መሳሪያ ማከማቻዎች እና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ነው የጠቆመው።
የቤሩት አውሮፕላን ማረፊያ ከጥቃቶቹ በኋላ አገልግሎቱን መቀጠሉ ተገልጿል።
በሌላ በኩል ሄዝቦላህ ወደ ሰሜናዊ እስራኤል በተኮሰው ሮኬት የአንድ እስራኤላዊ ህይወት ማለፉን የእስራኤል የህክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ሄዝቦላህ የቀድሞ መሪው ሀሰን ናስራላህ የተገደለበትን 40ኛ ቀን ትናንት ሲያስብ አዲሱ መሪ ናይም ቃሲም በቴሌቪዥን መግለጫ ሰጥተዋል። የሄዝቦላህ መሪ በንግግራቸው ቡድኑ ለተኩስ አቁም ንግግር ዝግጁ የሚሆነው “እስራኤል ወረራዋን ካቆመች ብቻ ነው” ማለታቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ሃማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በፈጸመ ማግስት ለፍልስጤማውያን አጋርነቱን ለመግለጽ በቴል አቪቭ ላይ የሮኬት እና ድሮን ጥቃት ማድረሱን የቀጠለው ሄዝቦላህ በእስራኤል በየእለቱ የአየር ጥቃት እየተፈጸመበት ቢሆንም “አሁንም አቅሜ አልተነካም” ብሏል።
እስራኤል በሊባኖስ በፈጸመችው ጥቃት ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል፤ ከ13 ሺህ 600 በላይ ደግሞ መቁሰላቸውን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።