ዩክሬን ወደ ሶሪያ ሰብአዊ ድጋፍ ለመላክ መዘጋጅቷን አስታወቀች
ኬቭ ከአሳድ አገዛዝ መውደቅ በኋላ ሶሪያን የማረጋጋቱን ሂደት ታግዛለች ብለዋል ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ
ዩክሬን በጦርነት ውስጥ ሆና 20 ሚሊየን ሰዎችን ከረሃብ መታደግ መቻሏንም ተናግረዋል
ዩክሬን በሶሪያ የምግብ ቀውስ እንዳይከሰት የሰብአዊ ድጋፍ ለመላክ መዘጋጀቷን አስታወቀች።
ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ከአለማቀፍ ተቋማት እና አጋሮች ጋር በመሆን ወደ ሶሪያ ድጋፍ የሚላክበት መንገድ እንዲመቻች ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል።
ዩክሬን ከአለማችን የምግብ እና ቅባት እህል አምራቾች ከቀዳሚዎቹ ተርታ ትሰለፋለች። ለበርካታ የመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ ሀገራትም ምርቶቿን ትልካለች። ኬቭ ለደማስቆ ግን ስንዴም ሆነ በቆሎ አትልክም።
ሶሪያ በበሽር አል አሳድ የስልጣን ዘመን የምግብ እህሎችን የምትሸምተው ከሩሲያ ነው።
ይሁን እንጂ ከክፍያ መዘግየት ጋር በተያያዘ ሞስኮ ወደ ደማስቆ የምትልከውን ስንዴ ማቆሟን ሬውተርስ የሩሲያ እና ሶሪያ ምንጮቹን ጠቅሶ አስነብቧል።
የአሳድ አገዛዝ መወገድን ተከትሎ ለ13 አመታት በጦርነት በቆየችው ሶሪያ የሰብአዊ ቀውስ እንዳይከተል ስጋት ተፈጥሯል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፥ "ሶሪያን ለመርዳትና የምግብ ቀውስን ለማስቀረት ዝግጁ ነው፤ ለዚህም "እህልፍ ከዩክሬን" የተሰኘውን የሰብአዊ ድጋፍ ፕሮግራም እንጠቀማለን" ብለዋል።
ኬቭ ምን ያህል ድጋፍ እንደምታደርግና በየትኛው መስመር ልታቀርብ እንዳሰበች ግን ማብራሪያ አልሰጡም።
ዜለንስኪ ሩሲያ በሶሪያ ለአመታት የተካሄደውን ጦርነት ማቀጣጠሏን በመጥቀስም አለማቀፉ ማህበረሰብ ለደማስቆ ሰላም በጋራ ይሰራ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።
ሩሲያ በየካቲት 2022 ወደ ዩክሬን ዘልቃ ከገባች በኋላ ኬቭ በጥቁር ባህር በኩል ለአለም ገበያ የምታቀርበው የግብርና ምርት መጠን በእጅጉ ቀንሷል።
በመንግስታቱ ድርጅትና በቱርክ አደራዳሪነት የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ ምርቶቿን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ብትጀምርም ስምምነቱ መራዘም ሳይችል ቀርቷል። ያም ሆኖ ዩክሬን በኦዴሳ ወደብ በኩል የግብርና ምርቶቿን እያቀረበች ነው ተብሏል።
ኬቭ በጦርነት ውስጥ ሆና በምታደርገው የሰብአዊ ድጋፍ 20 ሚሊየን ሰዎችን ከረሃብ መታደግ መቻሏን ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ተናግረዋል።