እስራኤል በተኩስ አቁም ጉዳይ ውይይት የሚያደርግ ቡድን ወደ ኳታር ልትልክ መሆኑን ገለጸች
ሀማስ ስምምነቱ ተግባራዊ በሆነበት የመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ታጋቾችን የለቀቀ ሲሆን እስራኤል እስከ እድሜ ልክ እስራት ፍርደኛ የነበሩ በርካታ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለቃለች
ሀማስ እስራኤል ከጋዛ ለቃ እንድትወጣና ዘላቂ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የሚፈልግ ሲሆን እስራኤል በአንጻሩ ሀማስን ጨርሶ ማጥፋት የዘመቻ ግቧ እንደሆነ በተደጋጋሚ መግለጿ ይታወሳል
እስራኤል በተኩስ አቁም ጉዳይ ውይይት የሚያደርግ ቡድን ወደ ኳታር ልትልክ መሆኑን ገለጸች።
እስራኤል በጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት ቀጣይ አተገባበር ዙሪያ ውይይት የሚያደርግ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ወደ ኳታር ለመላክ እየተዘጋጀች መሆኗን የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ቢሮ በዛሬው እለት አስታውቋል።
እስራኤል እና ሀማስ በደረሱት ለስድስት ሳምንታት በሚቆየው የመጀመሪያ ዙር የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት ታጋቾች በፍልስጤማውያን እስረኞች ተለውጠው የተለቀቁ ሲሆን ዛሬ የሚጀመረው ሁለተኛው ዙር ድርድር ደግሞ ጦርነቱን በዘለቄታዊነት ያስቆመዋል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።
ሀማስ ስምምነቱ ተግባራዊ በሆነበት የመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ታጋቾችን የለቀቀ ሲሆን እስራኤል እስከ እድሜ ልክ እስራት ፍርደኛ የነበሩ በርካታ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለቃለች።
ከተለቀቁት የእስራኤል ታጋቾች ውስጥ አምስቱ ሴት እስራኤላውያን ወታደሮች ናቸው።
በሁለተኛው ዙር ድርድር ሀማስ በእጁ ያሉትን ሁሉንም ታጋቾች እንዲለቅና እስራኤል ደግሞ ከጋዛ ጠቅልላ እንድትወጣ ንግግር ይደረጋል ተብሏል።
ሀማስ እስራኤል ከጋዛ ለቃ እንድትወጣና ዘላቂ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የሚፈልግ ሲሆን እስራኤል በአንጻሩ ሀማስን ጨርሶ ማጥፋት የዘመቻ ግቧ እንደሆነ በተደጋጋሚ መግለጿ ይታወሳል።
የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ለ15 ወራት በቆየው ጦርነት የፈራረሰችው ጋዛ መልሳ እስከምትገነባ ድረስ በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያን ወደ ግብጽና ጆርዳን ይዛወሩ የሚል አነጋጋሪ አስተያየት ባለፈው ወር ሰጥተዋል።
የፍልስጤም አስተዳደር ባለስልጣናትና እና የአረብ ሀገራት ይህን የትራምፕን ሀሳብ እንደማይቀበሉ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ ግልጽ አድርገዋል።
የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው መጠነሰፊ ጥቃት ከ47ሺ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል። እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት የዘር ማጥፋት ክስ አስተባብላለች።
ሀማስ ጥቅምት 7፣2023 በደቡብ እስራኤል ድንበር ጥሶ በመግባት 1200 ሰዎችን ከደገለ እና 250 ሰዎችን አግቶ መወሰዱን ተከትሎ ነበር ሀሰማስና እስራኤል ወደ አጠቃላይ ጦርነት የጠቡት።