የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ኬንያ ያቀረበችበትን ክስ አስተባበለ
የኬንያ ፖሊስ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን ኢላማ ያደረገ ዘመቻ በማርሳቢትና ኢሲዮሎ መክፈቱን አስታውቋል
ኬንያ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን በህገ ወጥ የጦር መሳሪያና አደዛዥ እጽ ዝውወርን ጨምሮ በሰዎች እገታ ከሳለች
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በኬንያ መንግስት የተከፈተበትን ዘመቻ ተከትሎ በሀገሪቱ የቀረበበትን ውንጀላ አስተባበለ።
የኬንያ ብሄራዊ ፖሊስ በማርሳቢትና ኢሲዮሎ አካባቢ በሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነጻት ሰራዊት ላይ ዘመቻ መክፈቱን ገልጿል።
ዘመቻው በተከታታይ የድንር ዘለል ወንጀሎች ተጠያቂ የሆነው የኦሮሞ ነጻት ሰራዊት ላይ ያነጣጠረ መሆኑንም ፖሊስ በመግለጫው አስታውቋል።
የኬንያ ፖሊስ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን በህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና አደንዛዥ እጽ ዝውውር፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የኮንትሮባንድ እቃዎች ንግድ፣ ህገ-ወጥ ማዕድን ማውጣት፣ የጎሳ ግጭቶችን በማነሳሳት እና ሰዎችን አግቶ ገንዘብ በመቀበል ወንጀሎች ይከሳል።
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በኬንያ ብሄራዊ ፖሊስ የተከፈተበትን ዘመቻ እና የቀረበበትን ክስ በማስተባበል በይፋዊ የኤክስ (ትዊተር) ገጽ ባጋራው መግለጫ፤ “የኬንያ ፖሊስ በማርሳቢት እና ኢሲዮሎ አካባቢዎች ስማቸው ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ተያይዘው የተነሱ ወንጀለኞችን ለማጥፋት እንቅስቃሴ መጀመሩን ሪፖርቶች ደርሰውኛል” ብሏል።
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እንቅስቃሴው በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ብቻ መሆኑን ባመላከተበት መግለጫው ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የደቡብ እዝ ሰራዊት አባላት በደቡብ ኦሮሚያ ውስጥ፤ ከ5% በታች የሆኑት ደግሞ በኬንያ ድንበር አካባቢ ይገኛሉ ብሏል።
በእነዚህ አካባቢዎች የሚያደርጋው እንቅስቃሴ የኬንያን ሉዓላዊነት ያገናዘበ መሆኑንም በመጥቀስ፤ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች የሚያውኩ የወንጀል ድርጊቶችን እንደሚያወግዝም አስታውቋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በመግለጫው “በሁለቱ ሀገራት የጋራ ድበር አካባቢ ወነጀለኞችን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ከኬንያ ባለስልጣናት ጋር ለመተባበር ፈቃደኞች ነን” ብሏል።
በሁለቱም ድንበር በኩል በአደንዛዥ እፅ፣ በሰው እና በማዕድናት ዝውውር ላይ የተሰማሩ የወንጀለኞች መረቦችን በሚገባ እናውቃለን ያለው ሰራዊቱ፤ ለዚህም በስም ያልጠቀሳቸውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የደህንነት ኃላፊዎችን ተጠያቂ አድርጓል።
“በማናቸውም አጋጣሚ ማንኛውም የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በዚህ የወንጀል ተግር ላይ ከተገኘ ጉዳዩን ለመፍታት እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን” ብሏል መግለጫው።
የኬንያ ፖሊስ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት በሚቀርብለት መረጃ እንዳይታለልና ጥንቃቄ እንዲያደርግም የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በመግለጫው አሳስቧል።
የኬንያ ብሄራዊ ፖሊስ ትናንት ሰኞ ጥር 26 በሰጠው መግለጫ "ወንጀለኞችን የማስወገድ ኦፕሬሽን" በማርሳቢትና ኢሲዮሎ ውስጥ በተለይም በሶሎሎ፣ ሞያሌ፣ ሰሜን ሆር እና መርቲ አካባቢዎች ተደብቀው የሚገኙ የኦሮሞ ነጻት ሰራዊት ወንጀለኞችን ለማጥፋት ያለመ መሆኑን አስታውቋል።
የኢትዮያ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ባለንት ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ወደ ናይሮቢ አቅንተው ከኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር መነጋራቸው ይታወሳል።
የኬንያው የብሔራዊ መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ኑረዲን ሐጂ በተገኙበት በተደረገው ውይይት ላይም ኢትዮጵያ እና ኬኒያ ሽብርተኝነትን ጨምሮ የተደራጁ ወንጀሎችን በጋራ መካላከል በሚችሉበት አግባብ ላይ ምክክርመደረጉም በወቅቱ ተነግሯል።