እስራኤል ዜጎቿ የጦር መሳሪያ እንዲታጠቁ የሚያበረታታ ውሳኔ ልታሳልፍ ነው
ፍልስጤማውያን ባለፉት ቀናት ባደረሷቸው ጥቃቶች ንጹሃን በመገደላቸው ነው ቴል አቪቭ ውሳኔውን የምታሳልፈው
ውሳኔው የጥቃት አድራሽ ቤተሰቦችን የማህበራዊ ዋስትና መብት መንጠቅንም ያካትታል ተብሏል
እስራኤል እያንዳንዱ ዜጋዋ የጦር መሳሪያ እንዲታጠቅ የሚያበረታታ ውሳኔ ልታሳልፍ መሆኑ ተነግሯል።
ከሰሞኑ በፍልስጤማውያን አማካኝነት ተፈጸሙ በተባሉ ግድያዎች ምክንያት ነው ቴል አቪቭ ዜጎቿን ለማስታጠቅ የሚያበረታታ ውሳኔን ለማሳለፍ የተዘጋጀችው።
“ንጹሃን መሳሪያ ከታጠቁ ራሳቸውን ከአደጋ ይጠብቃሉ” ብለዋል የእስራኤል የብሄራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ጂቪር ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ።
የሀገሪቱ የጸጥታ ካቢኔ በጉዳዩ ዙሪያ መክሮ ውሳኔ ለማሳለፍ ዛሬ እንደሚሰበሰብ ቢቢሲ ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከካቢኔ ስብሰባው አስቀድመው በሰጡት አስተያየት፥ “ጠንካራ” እና “ፈጣን” ውሳኔ ይተላለፋል ብለዋል።
ካቢኔው ከሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች መካከል የጥቃት አድራሽ ሰዎች ቤተሰቦች የማህበራዊ ዋስትና መብትን መግፈፍ የሚለው ተካቷል ነው የተባለው።
እስራኤል በዌስትባንክ ተጨማሪ ወታደሮችን እንድታሰማራም ካቢኔው ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።
በእየሩሳሌም ባለፈው አርብ ሰባት ሰዎች ለተገደሉበት ጥቃት በምስራቅ እየሩሳሌም የሚኖር ፍልስጤማዊ ተጠያቂ ተደርጓል።
በሌላ ጥቃትም እስራኤላዊ አባት እና ልጅን ተኩሶ ያቆሰለው የ13 አመት ፍልስጤማዊ ታዳጊ መሆኑን የእስራኤል ፖሊስ አስታውቋል።
ፖሊስ ከአርቡ ጥቃት ጋር በተያያዘ 42 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን፥ የጸጥታ ካቢኔው ዛሬ የሚያሳልፈው ውሳኔ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
የእስራኤል ወታደሮች ባለፈው ሃሙስ በዌስባንክ ጀኒን ዘጠኝ የታጠቁና ንጹሃን ዜጎችን ከገደሉ በኋላ ውጥረቱ መባባሱ የሚታወስ ነው።
ከጋዛ ሰርጥ ወደ እስራኤል የተተኮሰ ሮኬትም ለሰሞኑ ውጥረት መነሻ ተደርጎ ይወሰዳል።
የፈረንጆቹ አዲስ አመት ከገባ ወዲህ በዌስትባክን 30 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል።
ባለፈው ሳምንት በጀኒን ከተፈጸመው የ9 ፍልስጤማውያን ግድያ በኋላም የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ሙሃመድ አባስ ከእስራኤል ጋር የደህንነት ትብብራችን አቋርጠናል ማለታቸው ይታወሳል።
የሰሞኑ ውጥረት አሳሳቢነትን የጠቀሱት የመንግስታቱ ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረት የእስራኤልና ፍልስጤም መሪዎች ግጭቱን እንዲያረግቡት ጠይቀዋል።
እያንዳንዱን እስራኤላዊ መሳሪያ ማስታጠቅም “የመጨረሻው አማራጭ” እንጂ ሁነኛው መፍትሄ አይደለም ብለዋል።