ዩኔስ ወደ ትውልድ ቀዬው ሲያመራ 40 አመቱ ሙሉ ሲጠብቁት የቆዩትን እናት እና አባቱን ግን ማግኘት አይችልም
ለአራት አስርት አመታት በእስራኤል በእስር ላይ የቆየው ፍልስጤማዊ በዛሬው እለት ተፈቷል።
በፈረንጆቹ ጥር 6 1983 በወጣትነቱ በቁጥጥር ስር የዋለው ካሪም ዩኔስ፥ ጎልማሳ ሆኖ የነጻነት አየር መተንፈስ ጀምሯል።
የፍልስጤም የታራሚዎችና የቀድሞ ታራሚዎች ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፥ ዩኔስ በድንገት ነው ዛሬ ከእስር የተለቀቀው።
የእስራኤል የማረሚያ ቤት ሰራተኞች ለዩኔስ ቤተሰቦች መፈታቱን ሳያሳውቁ በቴል አቪቭ አቅራቢያ ራናና በተባለው አውራ ጎዳና ጥለውት መሄዳቸውንም ነው የገለጸው።
ዩኔስ በትውልድ መንደሩ አራ ደማቅ አቀባበል ይደረግለታል ተብሏል።
ካሪም ዩኔስ ማን ነው?
በእስራኤል ለረጅም አመት በመታሰር ክብረወሰን የያዘው ግለሰብ ካሪም ዩኔስ አሁን 66ኛ አመቱን ይዟል።
ከ40 አመት በፊት በቁጥጥር ስር ሲውል የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረ ሲሆን፥ የእስሩ ምክንያትም የፋታህ ንቅናቄ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆኗል የሚል ነው።
ጥር 6 1983 በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰቡ የጦር መሳሪያዎችን ይዞ በመገኘት እና የእስራኤልን ወታደር በመግደል ወንጀልም ተከሶ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ነበር።
በሂደት ግን እስራቱ ወደ 40 አመት ዝቅ ብሎለት የ14 ሺህ 610 ቀናት የእስር ቤት ቆይታውን ዛሬ አጠናቆ ነጻ ሆኗል።
የእስር ቤት ጨለማ ያቋረጠውን የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ከመቀጠል ያላገደው ካሪም ዩኔስ፥ ሌሎች ታራሚዎችንም በማስተማር እውቀት መዝራቱ ተነግሯል።
ዛሬ ከአራት አስርት በኋላ ነጻነቱን አውጆ ከእስር ቤት ሲወጣ ግን ነገሮች ሁሉ ተለዋውጠው ጠብቀውታል፤ አባቱ እና እናቱም አቅፈው አይስሙትም።
40 አመት ሙሉ በናፍቆት የጠበቁትን እናቱ ከወራት በፊት ህይወታቸው አልፏል። አባቱም በ2013 መሞታቸውን ነው አል አይን አል አክባሪያ ያስነበበው።
ዩኔስ በ1993 ከተፈረመው የኦስሎ ስምምነት አስቀድሞ የታሰረ በመሆኑ ይፈታ ዘንድ ከፍልስጤም በኩል ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም የእስር ጊዜውን ማጠናቀቅ ግድ ብሎታል።