እስራኤል በስህተት በፈጸመችው ጥቃት ሶስት ታጋቾች መገደላቸውን ተከትሎ የተቃውሞ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው
እስራኤል በሃማስ የታገቱ ሰዎችን ለማስለቀቅ አዲስ ድርድር እየተካሄደ መሆኑን አረጋገጠች።
የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት (ሞሳድ) ሃላፊ ዴቪድ ባርኔይ ከኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ቢን አብዱርሃማን ጃሲም አልታኒ ጋር በአውሮፓ መምከራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የእስራኤልና ኳታር ከፍተኛ ባለስልጣናት ከጋዛው ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ ያደረጉት ምክክር በየትኛው የአውሮፓ ሀገር እንደተካሄደ አልተገለጸም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ስለድርድሩ ማረጋገጫ ቢሰጡም ዝርዝር ጉዳዮችን አላነሱም።
ኳታር ለታማስ በምታደርገው ድጋፍና ከኢራን ጋር ባላት ግንኙነት በማደራደር ሚናዋ ከእስራኤል በኩል ቅሬታ ቢቀርብም ዶሃ ለሰባት ቀናት የዘለቀ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ማድረጓ ይታወሳል።
“ለተደራዳሪዎች ግልጽ መመሪያ ሰጥቻለሁ፤ ድርድሩ የሚወሰነው በሃማስ ላይ በምናሳድረው ጫና ነው” ያሉት ኔታንያሁ፥ የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት ጦርነት የሚጠናቀቀው ጋዛን ከጦር ቀጠና ነጻ ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው ብለዋል።
ጦርነቱ ታጋቾችን የማስለቀቅ እና ሃማስን ሙሉ በሙሉ የመደምሰስ ግብ እንዳለው ቢገልጹም በፍልስጤማውያን ላይ እየደረሰ የሚገኘው ድብደባ አለማቀፍ ትችት እያስነሳባቸው ነው።
እስራኤል ሶስት ታጋቾችን በስህተት በፈጸመችው ጥቃት መግደሏን ተከትሎም እስራኤላውያን ቁጣቸውን በማሰማት ላይ ናቸው።
በቴል አቪቭ በተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎችም ታጋቾች በፍጥነት የሚለቀቁበት መንገድ እንዲፈለግ ተጠይቋል።
ሃማስ በኳታር አደራዳሪነት እንደአዲስ በተጀመረው ድርድር እንዳልተሳተፈ ገልጿል።
“በህዝባችን ላይ የታወጀው ወረራ ሙሉ በሙሉ ካልቆመ በየትኛውም ድርድር አልሳተፍም” ማለቱም ተዘግቧል።
በእስራኤል የአየር እና ምድር ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ19 ሺህ በላይ መድረሱን የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።