በጋዛው ጦርነት 13 ሺህ የሚጠጉ “ሽብርተኞች” ተገድለዋል - ኔታንያሁ
በጦርነቱ ከተቀጠፉት መካከል ከ70 በመቶ በላዩ ህጻናትና ሴቶች ናቸው ያለው ሃማስ በበኩሉ፥ ኔታንያሁ ያልተገኘ ድልን አጋነው በማቅረብ ተጠምደዋል ብሏል
እስራኤል ሃማስን ለመደምሰስ በራፋህ የማደርገው ዘመቻ ወሳኝ ነው ብላለች
እስራኤል በጋዛ ከሃማስ ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት ከተገደሉ ፍልስጤማውያን መካከል 13 ሺህ የሚጠጉት “ሽብርተኞች” ናቸው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጀርመኑ ሚዲያ አክስል ስፕሪንገር ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው አምስት ወራት ባስቆጠረው ጦርነት የተገደሉ ታጣቂዎችን ቁጥር የገለጹት።
የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እስካሁን በጦርነቱ ህይወታቸው ካለፈ 31 ሺህ ፍልስጤማውያን ውስጥ ምን ያህሉ ንጹሃን እና ታጣቂዎች እንደሆኑ ለይቶ አላስቀመጠም።
ሃማስ በበኩሉ ከ72 በመቶ በላዩ ሟቾች ህጻናትና ሴቶች መሆናቸውን በመጥቀስ በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር በኩል የቀረበው አሃዝም “ያልተገኘ ድልን” ለማወጅ የሚያደርጉት ጥረት ማሳያ ነው ብሏል።
ኔታንያሁ ፖለቲኮ እና ቢልድ ጋዜጣን ከሚያስተዳድረው አክስል ስፕሪንገር ጋር በነበራቸው ቆይታ ግን “ለድል ተቃርበናል፤ ሃማስን ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ የምናካሂደው ዘመቻ ወሳኝ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በራፋህ የሚካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ በሳምንታት ውስጥ ሽብርተኞችን ይደመስሳል ማለታቸውንም ቢልድ ጋዜጣ አስነብቧል።
ይሁን እንጂ በጋዛ ነገሮች እንዳልጠበቁት የሆነባቸው ኔታንያሁ በሳምንታት እጨርሰዋለው ያሉት ሃማስን የመደምሰስ ዘመቻ አምስት ወራት ተቆጥሮም አልተጠናቀቀም።
በራፋህ የሚጀመረው ጦርነትም የፍልስጤማውያንን ሰቆቃ ከማብዛት ባለፈ በአጭር ጊዜ ድል ይገኝበታል ተብሎ እንደማይጠበቅ ሬውተርስ ዘግቧል።
አሜሪካም ከጋዛ ህዝብ ከግማሽ በላዩ በሰፈሩበት ራፋህ የሚደረግ ጦርነት አደገኛ ነው ብላለች።
ፕሬዝዳንት ባይደን የራፋህ ወረራ የአሜሪካ ቀይ መስመር ነው ወይ ተብለው ተጠይቀው፥ “አዎ ቀይ መስመር ነው፤ ግን እስራኤልን እንዲሁ አልተዋትም” ማለታቸው ግልጽ አቋም ለመያዝ መቸገራቸውን ያሳያል ተብሏል።
ኔታንያሁ ግን “ቀይ መስመር አለን፤ ይህ መስመር የጥቅምት ሰባቱ ጥቃት ድጋሚ እንዳይከሰት ማድረግ ነው፤ በድጋሚ አይከሰትም” በማለት የራፋሁ ጦርነት አይቀሬ መሆኑን አመላክተዋል።
እስራኤል የሃማስ ታጣቂዎች በራፋህ መሽገዋል በሚል ልትጀምረው ያሰበችው ጦርነት ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ እንደሚያስከትል አለማቀፍ ተቋማት ቢያስጠነቅቁም ቴል አቪቭ ዝግጅቷን ቀጥላለች።