አንድ አመት በጦርነት ውስጥ ያሳለፈችው እስራኤል የ66 ቢሊየን ዶላር ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንደደረሰባት ተገለጸ
ከጋዛው ጦርነት ጋር በተያያዘ ያስተናገደችው ምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራ በ1973 ከግብጽ ጋር ባደረገችው ጦርነት ከደረሰባት ሊበልጥ እንደሚችል ተነግሯል
እሰራኤል ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖውን ለመከላከል የታክስ ጭማሪ ልታደርግ እንደምትችል ይጠበቃል
አንድ አመት በጦርነት ውስጥ ያሳለፈችው እስራኤል የ66 ቢሊየን ዶላር ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንደደረሰባት ተገለጸ።
አንድ አመትን ያሰቆጠረው የጋዛ ጦርነት ካስከተለው የሰብአዊ ጉዳት ባለፈ በኢኮኖሚ ላይ ያደረሰው ኪሳራ ከፍተኛ እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡
እስራኤል በፍልስጤም እያደረሰችው ከሚገኘው መጠነ ሰፊ ጥቃት ባለፈ በቅርብ ሳምንታት በሊባኖስ እና በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ሀገራት የምትፈጽመው ጥቃት በኢኮኖሚያዋ ላይ ተጽእኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡
እስካሁን ባለውም ሀገሪቱ 66 ቢሊየን ዶላር ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንደደረሰባት የተነገረ ሲሆን፤ የጦርነቱ መራዘም በ1973 ከግብጽ ጋር ባደረገችው ጦርነት ለ10 አመታት ከደረሰባት ምጣኔ ሀብታዊ ተጽእኖ ሊበልጥ እንደሚችል ነው የተነገረው፡፡
የእስራል የፋይናንስ ሚንስተር ቤዛለል ስሞትሪች ሀገሪቱ በታሪኳ ውዱ የሆነውን ጦርነት እያካሄደች ነው ብለዋል፡፡
ሲኤንኤን ለንባብ ባበቃው ትንታኔ አሁን ባለው ሁኔታ ቴልአቪቭ ኢኮኖሚያዊ ጫናውን የመቋቋም አቅም ቢኖራትም ጦርነቱ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ግን ተጽእኖው ከሀገሪቱ አልፎ ለመካከለኛው ምስራቅም እንደሚተርፍ አስነብቧል፡፡
የቀድሞው የእስራኤል የማዕከላዊ ባንክ ገዢ ካርኒት ፍለግ እንደተናገሩት መንግስት በጦርነቱ ተጽእኖ ምክንያት የሚያጋጥመውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመቋቋም የታክስ እና ሌሎች የገቢ ማግኛ መነገዶች ላይ ጭማሪ ሊያደርግ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ለኢንቨስትመንት እና መሰረተ ልማት የሚመድመውን ገንዘብ በመቀነስ የመከላከያውን አቅም ማጠናከር ፣ ወታደራዊ ወጪዎችን መሸፈን ላይ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
በአሁኑ ወቅት ለወታደራዊ ወጭ ፣ በሰሜን እና ደቡብ በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች መጠለያ እና የምግብ እንዲሁም ሌሎች ወጪዎች ፈሰስ የሚያደርገው ገንዘብ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ 12 በመቶውን እንደሚሸፍን መረጃዎች አመላክተዋል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ባለፈው ወር ባወጣው ሪፖርት የግጭቱ መራዘም እንዲሁም እያሳተፋቸው የሚገኙ አካላት መበራከት ከቀጠናው አልፎ በአለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ እክል ሊፈጥር እንደሚችል አስጠንቅቆ ነበር፡፡
በተለይ የኢራን እና የየመኑ ሀውቲ ተሳትፎ እያደገ መምጣት በቀይ ባህር እና በሆርሙዝ ሰርጥ የሚኖረውን የንግድ እና የነዳጅ እንቅስቃሴ በማስተጓጎል በሸቀጦች ላይ አሁን ካለው የሚከፋ የዋጋ ጭማሪን ሊያስከትል እንደሚችል አሳስቧል፡፡
እስራኤል ለሁለት ሳምንታት ከፍተኛ የአየር ላይ ጥቃት እየፈጸመችባት የምትገኘው ሊባኖስ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ እድገቷ በአምስት በመቶ ሊያሽቆለቁል ይችላልም ነው የተባለው፡፡