እስራኤል የምትሰጠው ምላሽ "መካከለኛው ምስራቅን ይቀይራል"- ጠቅላይ ሚኒስትር ንታንያሁ
እስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ውስጥ ከገቡ ዛሬ አራተኛ ቀናቸውን አስቆጥረዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ንታንያሁ እስራኤል ለደረሰባት ያልተጠበቀ እና ዘርፈ ብዙ ጥቃት የምትሰጠው ምላሽ "መካከለኛው ምስራቅን" ይቀይራል ብለዋል
እስራኤል ከጋዛ ለተቃጣባት ጥቃት የምትሰጠው ምላሽ የመካከለኛው ምስራቅ ሁኔታን እንደሚቀይረው ገለጸች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ንታንያሁ እስራኤል ለደረሰባት ያልተጠበቀ እና ዘርፈ ብዙ ጥቃት የምትሰጠው ምላሽ "መካከለኛው ምስራቅን" ይቀይራል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በደቡባዊ እስራኤል በሀማስ ያልተጠበቀ ጥቃት የደረሰባቸውን ከተሞች ከንቲባዎችን በሰበሰቡበት ወቅት ነው።
የእስራኤል ምላሽ መካከለኛው ምስራቅን በምን መልኩ እንደሚቀይረው ግን ጠቅላይ ማኒስትሩ አላብራሩም።
ሀማስ ከጋዛ ሮኬቶች በማስወንጨፍ እና በታጣቂዎቹ የእስራኤልን ድንበር በመጣስ ባደረሰው "ከባድ እና ያልተጠበቀ" ጥቃት ሳቢያ እስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ውስጥ ከገቡ አራተኛ ቀናቸውን አስቆጥረዋል።
ይህ ጥቃት በ50 አመታት ውስጥ ሀማስ ከሰነዘራቸው ጥቃቶች ውስጥ እጅግ ከባዱ መሆኑ ተገልጿል።
የሀማስን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በሀማስ መቀመጫ በሆነችው ጋዛ ላይ ከባድ የአየር ጥቃት እያደረሰች ነው፤ጋዛን በመክበብ ጥቃት አድራሾችንም ለመግደል ወስናለች።
እስራኤል ጋዛን ለመክበብ በምታደርገው ጥረት በደቡባዊ እስራኤል ከፍተኛ ጦር አሰማርታለች።
እስካሁን በጦርነቱ በእስራኤል 900 ሰዎች የሞቱ ሲሆን በጋዛ በኩል ደግሞ 700 ሰዎች ተገድለዋል።
አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን ሀገራት ሀማስን በማውገዝ እስራኤልን እንደሚደግፉ ባወጧቸው መግለጫዎች ገልጸዋል።
ሩሲያ እና የአረብ ሀገራት በአንጻሩ ማንንም ሳያወግዙ ግጭቱ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
ሀማስ ከእስራኤል ጋር ለመነጋገር ፍቃደኝነቱን ቢገልጽም ጋዛን ለመክበብ እየተንቀሳቀሰች ያለችው እስራኤል ማጥቃቷን ቀጥላለች።