አሜሪካና ብሪታንያ በየመን 8 የሃውቲ ታጣቂዎች ይዞታዎችን መምታታቸውን ገለጹ
በአየር ጥቃቶቹ የቡድኑ የምድር ውስጥ የመሳሪያ ማከማቻዎች መውደማቸውንም ነው ያስታወቁት
አሜሪካ በየመን ስምንተኛውን የአየር ጥቃት ብትፈጽምም ሃውቲዎች በቀይ ባህር በሚጓዙ መርከቦች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት አልቆመም
አሜሪካና ብሪታንያ በየመን ስምንት የሃውቲ ታጣቂዎች ይዞታዎችን መምታታቸውን ገለጹ።
የአየር ጥቃቶቹ የቡድኑን የምድር ውስጥ የመሳሪያ ማከማቻዎችና የሚሳኤል እና ቅኝት አቅሙን ማዳከም ኢላማ ያደረጉ ናቸው ብሏል ፔንታጎን።
የአሜሪካና ብሪታንያን የየመን የአየር ጥቃት አውስትራሊያ፣ ባህሬን፣ ካናዳና ኔዘርላንድስ መደገፋቸውንም ነው ስድስቱ ሀገራት ያወጡት የጋራ መግለጫ ያሳየው።
ከአሜሪካ ግዙፍ የጦር መርከብ ላይ የተነሱ አውሮፕላኖች ከ25 እስከ 30 የሚደርሱ መሳሪያዎችን መተኮሳቸውን ሬውተርስ ስማቸውን ያልጠቀሳቸውን የአሜሪካ ወታደራዊ አዛዥ ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
አሜሪካ ካለፈው ወር ጀምሮ በየመን የሃውቲ ታጣቂዎች ይዞታን ስትደበድብ የትናንቱ ስምንተኛው ሲሆን፥ ከብሪታንያ ጋር በቅንጅት የፈጸመችው ሁለተኛው ጥቃት ነው ተብሏል።
ከአየርና ከባህር ላይ የተቃጡት ጥቃቶች የሃውቲዎችን አቅም ማዳከሙ ቢገለጽም ቡድኑ አሁንም ድረስ ጥቃት ማድረሱን አላቆመም።
ባለፈው ሳምንትም የአሜሪካ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ያነጣጠሩ ሁለት ጸረ መርከብ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ተኩሶ በመርከቧ አቅራቢያ መውደቃቸው ይታወሳል።
የአሜሪካ መራሹ የየመን ጥቃትም ሆነ የቀይ ባህር ቅኝት ግብረሃይሉ የአለማችን ከ10 በመቶ በላይ ሸቀጦች መተላለፊያውን መስመር ደህንነት ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ አልቻለም።
በርካታ የመርከብ ኩባንያዎችም ከቀይ ባህር ይልቅ ረጅሙን የኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ መስመር መጠቀማቸውን ቀጥለዋል ነው የተባለው።
ዋሽንግተን እና አጋሮቿ በበኩላቸው ቡድኑ በቀይ ባህር ጥቃቱን ካላቆመ “ራሳችን ለመከላከል” የምንወስደውን እርምጃ እንቀጥላለን ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ባለፈው ሳምንትም አሜሪካ የየመኑን ቡድን ዳግም በአለማቀፍ ሽብርተኞች ዝርዝር ማካተቷ ይታወሳል።