በጥቃቱ የአሜሪካ እና ኢራቅ ወታደሮች መጎዳታቸው ተገልጿል
አሜሪካ በኢራቅ ያለው የጦር ማዘዣ በሚሳኤል መመታቱን አመነች፡፡
የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት አሁንም መቋጫ ያልተገኘለት ሲሆን አሜሪካ ለእስራኤል በይፋ ድጋፍ ማድረጓን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ የጦር ማዘዣዎች የጥቃት ኢላማ ተደርገዋል፡፡
በኢራቅ ያለው አይን አል አሳድ የተሰኘው የጦር ማዘዣዋ በተደጋጋሚ በተተኮሰ ባልስቲክ ሚሳኤል መመታቱን አስታውቃለች፡፡
ሮይተርስ ስማቸው ያልተጠቀሰ የፔንታጎን ባለስልጣንን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች በኢራቅ በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ማዘዣ ላይ ጥቃት አድርሰዋል ብሏል፡፡
ወደ ጦር ማዘዣው ከተተኮሱ ሚሳኤሎች መካከል አብዛኛው ኢላማውን እንዳይመታ ማድረግ ተችሏል የተባለ ሲሆን የተወሰኑት ግን ጥቃት እንዳደረሱም ተገልጿል፡፡
አሜሪካ በሶማሊያ ወደብ ዘመቻ ላይ የነበሩ መርከበኞቿ እንደጠፉባት ገለጸች
በዚህ ጥቃትም የአሜሪካ እና የኢራቅ ወታደሮች እንደቆሰሉ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ከአካላዊ ጉዳት ባለፈም በርካታ የአሜሪካ ወታደሮች ለከባድ የአዕምሮ ስቃይ እንደተዳረጉ የተገለጸ ሲሆን ህክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ከታጣቂዎቹ በተተኮሰው ሚሳኤል የደረሰው ጉዳት እየተጣራ ነው የተባለ ሲሆን የጦር ማዘዣው ከእስራኤል-ሐማስ ጦርነት በኋላ 58 ጊዜ ጥቃት ተሞክሮበታልም ተብሏል፡፡
እንዲሁም በሶሪያ ያለው የአሜሪካ ተመሳሳይ የጦር ማዘዣ 83 ጊዜ ጥቃት የተሞከረበት ሲሆን አሜሪካም የአጸፋ እርምጃ ስትወስድ ቆይታለች፡፡
አሜሪካ በሶሪያ እና ኢራቅ የአይኤስ ሽብርተኛ ታጣቂዎችን ለመዋጋት በሚል ከ3 ሺህ በላይ ወታደሮች አሏት፡፡
ኢራቅ መሬቷ የአሜሪካ እና ኢራን የውጊያ ስፍራ በመሆኑ እንዳሳሰባት የገለጸች ሲሆን በግዛቷ ያለው የአሜሪካ ጦር ከሀገሯ እንዲወጣ ግፊት በማድረግ ላይ መሆኗን አስታውቃለች፡፡
አሜሪካ በበኩሏ ጦሯን ወደ ኢራቅ ያስገባችው በቀረበላት ግብዣ መሰረት መሆኑን ገልጻ ጦሯን የማስወጣት እቅድ እንደሌላትም ገልጻለች፡፡