የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ የፍልስጤምን ሙሉ አባልነት ደገፈ
ፍልስጤም 194ኛዋ የመንግስታቱ ድርጅት አባል እንድትሆንም የጸጥታው ምክርቤት ውሳኔውን በድጋሚ እንዲያጤን ጠይቋል
አሜሪካ እና እስራኤልን ጨምሮ ዘጠኝ ሀገራት የፍልስጤምን ሙሉ አባልነት ተቃውመዋል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የፍልስጤምን የድርጅቱ ሙሉ አባልነት ደገፈ።
ጠቅላላ ጉባኤው ትናንት ባካሄደው ስብሰባ ፍልስጤም 194ኛዋ የተመድ አባል ሀገር እንድትሆን ድጋፉን ሰጥቷል።
143 ሀገራት ለውሳኔ ሃሳቡ ድጋፋቸውን የሰጡ ሲሆን፥ 25 ሀገራት ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል።
አሜሪካና እስራኤልን ጨምሮ ዘጠኝ ሀገራት ደግሞ የፍልስጤምን ሙሉ የተመድ አባልነት እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በአብላጫ ድምጽ ለፍልስጤም የአባልነት ጥያቄ ድጋፉን ቢሰጥም 15 አባላት ያሉት የጸጥታው ምክርቤት ወሳኝ ድርሻ አለው።
በምክርቤቱ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላት አሜሪካም ባለፈው ወር የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ ማድረጓ አይዘነጋም።
“እኛ ሰላምና ነጻነትን እንፈልጋለን፤ የድጋፍ ድምጻችሁ የፍልስጤም ህልውና ይቀጥል ማለት ነው” ያሉት በመንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤም አምባሳደር ሪያድ ማንሱር፥ የአባልነት ጥያቄው ማንንም የሚጎዳ አለመሆኑን አብራርተዋል።
በተመድ የእስራኤል አባሳደር ጊላድ ኤርዳን በበኩላቸው ጠቅላላ ጉባኤው ከተመድ መቋቋሚያ ቻርተር ያፈነገጠ ውሳኔ እያሳለፈ መሆኑን ገልጸዋል።
“አብዛኞቻችሁ ይሁዲ ጠል ስለሆናችሁ ፍልስጤማውያን ሰላም አፍቃሪ ህዝብ አለመሆናቸው አያሳስባችሁም” ሲሉም ጠንከር ባሉ ቃላት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ትናንት ያሳለፈው ውሳኔ ፍልስጤም በክርክሮች እና አጀንዳ ቀረጻ እንድትሳተፍና በተለያዩ ኮሚቴዎች እንድትወከል ተጨማሪ መብትን የሰጠ ነው።
ሙሉ አባልነቷ በጸጥታው ምክርቤት እስካልጸደቀ ድረስ ግን በተለያዩ ውሳኔዎች ላይ ድምጽ መስጠት አትችልም።
ከ2012 ጀምሮ የመንግስታቱ ድርጅትን በታዛቢነት የተቀላቀለችው ፍልስጤም የድርጅቱ ሙሉ አባል እንድትሆን ጥረታችን ይቀጥላል ብለዋል ፕሬዝዳንት ሙሃሙድ አባስ።
በርካታ የአውሮፓ ሀገራትም ለፍልስጤም ነጻ ሀገርነት እውቅና ለመስጠት እየተዘጋጁ ነው መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል።
ስፔን፣ አየርላንድ፣ ስሎቫኒያ እና ማልታ ለፍልስጤም እውቅና እንደሚሰጡ የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሬል ተናግረዋል።
ከመንግስታቱ ድርጅት 193 አባል ሀገራት 139ኙ ለፍልስጤም ሀገርነት እውቅና መስጠታቸውን የሬውተርስ ዘገባ ያመላክታል።