ትራምፕ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ ስልጣን መልቀቃቸውን ማሳወቃቸውን ተከትሎ ካናዳ ወደ አሜሪካ እንድትጠቃለል ጥሪ አቅርቡ
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ካናዳ እና አሜሪካ ቢቀላቀሉ ታላቅ ሀገር መመስረት ይችላሉ ብለዋል
በዜጎች ከፍተኛ ተቀባይነት ያጡት የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር በትላንትናው ዕለት ከስልጣን መልቀቃቸውን ይፋ አድርገዋል
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ከስልጣን ከለቀቁ በኋላ ካናዳ በይፋ 51ኛዋ የአሜሪካ ግዛት እንድትሆን ሀሳብ አቅርበዋል።
ትሩዶ በሊበራል ፓርቲ ውስጥ ያለውን “ውስጣዊ ሽኩቻ” በመጥቀስ ሰኞ እለት ከሀላፊነት መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።
ፓርቲያቸው ከጥቅምት መጨረሻ በፊት በሚደረገው አዲስ ፓርላመንታዊ ምርጫ ፓርቲውን የሚወክል አዲስ መሪ እስከሚሾም ድረስ ቱሩዶ በጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ይቆያሉ፡፡
ትራምፕ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን መልቀቅ በተሰማ በሰአታት ውስጥ ትሩዝ በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ “በርካታ ከናዳውን የአሜሪካ አካል መሆንን ይፈልጋሉ” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም “ካናዳ ከአሜሪካ ጋር ከተቀላቀለች የታሪፍ ጭማሪ አይኖርም ፣ ካናዳውያንም ዝቅተኛ ቀረጥ ይከፍላሉ፤ እንዲሁም በቋሚነት በዙሪያቸው ካሉት የሩሲያ እና የቻይና መርከቦች ስጋት ሙሉ በሙሉ ነጻ ይሆናሉ” ሲሉ ትራምፕ አክለዋል።
ከካናዳ እና ከሜክሲኮ በሚያልፉ ዕቃዎች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ ጭማሪ እንደሚያደርጉ ትራምፕ ዝተዋል፡፡
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ወደ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ፍሎሪዳ መኖሪያ ቤት በማቅናት በጉዳዩ ላይ በቀጥታ ለመወያየት ሞክረዋል ።
ሁለቱ መሪዎች በታደሙበት የእራት ግብዣ “አስተዳዳሪ” ሲሉ ትሩዶን በቀልድ መልክ የጠሯቸው ትራምፕ ካናዳ 51ኛው የአሜሪካ ግዛት መሆን አለባት ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡
ትራምፕ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ካናዳ በሊበራል እና በወግ አጥባቂ የምትመራ ወደ ሁለት ሀገርነት ልትከፈል ትችላች ሲሉ በተለያዩ አጋታሚዎች ላይ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የዴንማርክ ግዛት የሆነችውን በሰሜን ምስራቅ የካናዳ የባህር ዳርቻ ላይ የምትገኘውን የአርክቲክ ደሴት ግሪንላንድን ወደ አሜሪካ ለማጠቃለል እንደሚፈልጉም መናገራቸው ይታወሳል፡፡