ተመድ እስራኤል የጋዛ ጤና ተቋማትን አውድማለች ሲል ከሰሰ
"ቢሮው "በጋዛ በጤና ተቋማት ላይ የደረሰው ውድመት፣ በታካሚዎች፣ በሰራተኞች እና በሌሎች ንጹሃን ላይ የደረሰው ግድያ ለአለምአቀፍ ህግ እና ሰብአዊ መብቶች ካለ ንቀት የመጣ ነው"ብሏል
እስራኤል ቢሮው ያወጣውን ሪፖርት እንደማትቀበለው ገልጻለች
የተመድ የሰብአዊ መብቶች ቢሮ እስራኤል የጋዛ ጤና ተቋማትን አውድማለች ሲል ከሰሰ።
እስራኤል በፍልስጤሟ ጋዛ ግዛት የሚገኙ የጤና ተቋማትን ማውደሟን እና የእስራኤል አለምአቀፍ ህግን ማክበር ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ መግባቱን የተመድ የሰብአዊ መብት ቢሮ ማክሰኞ እለት ገልጿል።
ከጥቅምት 12፣2013- ሀምሌ 30፣2024 ድረስ ያለውን ጥቃት የመዘገበው ባለ 23 ገጽ ሪፖርት ሀማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከሰነዘረበት ከጥቅምት 7፣2023 ጀምሮ በጋዛ የተፈጸመው ጥቃት ፍልስጤማውያንን የጤና ተደራሽነት በእጅጉ እንዲጎዳ ማድረጉን ደምድሟል።
"በጋዛ በጤና ተቋማት ላይ የደረሰው ውድመት፣ በታካሚዎች፣ በሰራተኞች እና በሌሎች ንጹሃን ላይ የደረሰው ግድያ ለአለምአቀፍ ህግ እና ሰብአዊ መብቶች ካለ ንቀት የመጣ ነው"ብሏል ቢሮው።
በተመድ የቬኔቫ ቢሮ የእስራኤል ቋሚ ተወካይ ዳኒኤል ሜሮን በሪፖርቱ የተካተቱት መረጃዎች የተፈበረኩ ናቸው ሲሉ አጣጥለዋል። ተወካዩ በኤክስ ገጻቸው እስራኤል በአለምአቀፍ ህግ መሰረት እንደምትንቀሳቀስ፣ ንጹሃንን ኢላማ እንደማታደርግ የገለጹ ሲሆን ሀማስ ሆስፒታሎቹን "ለሽብር ተግባር" እየተጠቀመ ነው ሲሉ ከሰዋል።
የእስራኤል ጦር ሀማስ ሆስፒታሎችን ለማዘዣ ጣቢያነት እየተጠቀመባቸው ነው ሲል ይከሳል። የተመድ ሪፖርትር እንዲህ አይነት ክስ መኖሩን ጠቅሶ፤ ይህን ለማረጋገጥ የሚያስችል መረጃ ግን የለም ብሏል።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት እስራኤል በጋዛ እያካሄደችው ያለው ወታደራዊ ዘመቻ ከአለም ጤና ድርጅት ተቃውሞ አስነስቶባታል።
ሪፖርቱ የቆሰሉ እና የታመሙ ሰዎች ያሉባቸው ሆስፒታሎች በቀጥታ መጠቃታቸውን እና ይህም የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል ገልጿል።
ሪፖርቱ በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙት የመብት ጥሰቶች በሰብአዊነት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ጋር የሚስተካከሉ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።
እስራኤል ግን ይህን አትቀበልም። ተመድ እንደገለጸው የእስራኤል ጦር የንጹሃን ጥቃትን ለማስቀረት እና የእርዳታ መስተጓጎልን ለማስቀረት በርካታ እርምጃዎች ወስጃለሁ የሚል ምላሽ ለሪ ሰጥቷል ብሏል።