ኢሳም አቡ ሩክባ ሃማስ በእስራኤል ላይ የድሮን ጥቃቶችን ሲፈጽም ዋነኛ አቀናባሪው ነበር ተብሏል
እስራኤል የሃማስን የአየር ሃይል መሪ ኢሳም አቡ ሩክባ መግደሏን አስታወቀች።
የእስራኤል ጦር ከሀገሪቱ የደህንነት ቢሮ (ሺን ቤት) ጋር በመተባበር ኢሳም አቡ ሩክባን በአየር ጥቃት መግደሉን ይፋ አድርጓል።
የሃማስን የአየር ላይ ጥቃቶች ይመራ የነበረው ኢሳም አቡ ሩክባ ማን ነው?
ኢሳም አቡ ሩክባ ሃማስ ከሶስት ሳምንት በፊት በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ሲፈጽም ቁልፍ ስራን ከከወኑ የቡድኑ መሪዎች መካከል አንዱ ነው።
በተለይም የሃማስ ታጣቂዎች ወደ እስራኤል በፓራሹት ዘልቀው በመግባት ጥቃት እንዲፈጽሙ አድርጓል ነው የተባለው።
ሃማስ በደቡባዊ እስራኤል በሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) የፈጸማቸውን ጥቃቶች መምራቱን የእስራኤል ጦር ገልጿል።
የእስራኤልን የድንበር ጥበቃ እና የአየር መቃወሚያዎችን በመምታትም ከ1 ሺህ 400 በላይ እስራኤላውያን እና የውጭ ሀገር ዜጎች የተገደሉበትን ጥቃት መርቷልም ብሏል ጦሩ።
የሃማስ ድሮኖች፣ ፓራሹቶችና የአየር መቃወሚያ ስርአቶች የሚቆጣጠረው እና የሚመራው ኢሳም አቡ ሩክባ መገደልም የቡድኑን የአየር ላይ ጥቃት እንደሚያዳክመው በእስራኤል ዘንድ ታምኗል።
የእስራኤል ጦር ከሁለት ሳምንት በፊትም የሃማስን የቀድሞ የአየር ሃይል መሪ ሙራድ አቡ ሙራድ መግደሉን ማሳወቁ ይታወሳል።
ሃማስ ስለኢሳም አቡ ሩክባ ግድያ እስካሁን ምንም ማረጋገጫ አልስጠም።
እስራኤል በጋዛ በአየር እና በምድር የምትፈጽመውን ጥቃት ማጠናከሯን ተከትሎ የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ “ቃሳም ብርጌድ” በቤት ሃኑን ከተማ ከባድ ውጊያ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።
ቡድኑ በሙሉ ሃይሉ የእስራኤልን ጦር እንደሚዋጋም ዝቷል።
ሶስተኛ ሳምንቱን በያዘው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ህይወታቸው ያለፈ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ7 ሺህ ተሻግሯል።