የአለም ባንክ ኡጋንዳ በተመሳሳይ ጾታ ዙርያ ያወጣችውን ጠንካራ ህግ የማታሻሽል ከሆነ የገንዘብ ድጋፍ እንደማያደርግ ገለጸ
ባንኩ ሀገሪቷ ባለፈው አመት ያወጣቸውን ጠንካራ ህግ ቀለል እንድታደርግ እያግባባ እንደሚገኝ ተሰምቷል
ኡጋንዳ ባሳለፍነው አመት ያወጣችው ህግ ከተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት የሚፈጽም የትኛውንም አካል በእድሜ ልክ እስራት የሚቀጣ ነው
የአለም ባንክ ኡጋንዳ በተመሳሳይ ጾታ ዙርያ ያወጣችውን ጠንካራ ህግ የማታሻሽል ከሆነ የገንዘብ ድጋፍ እንደማያደርግ ገለጸ።
የአለም ባንክ ኡጋንዳ የፀረ ግብረ ሰዶማውያን ህጎችን የምታቃልል ከሆነ ለሀገሪቱ የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ እንደገና እንዲቀጥል ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
የአለም ባንክ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት ካማፓላ ባሳለፍነው አመት ከተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ጋር በተገናኘ ያወጣቻቸው ጥብቅ ህጎች ላይ ማሻሻያ የምታደርግ ከሆነ ባንኩ የሀገሪቷን ፕሮጄክቶች ለመደግፍ የገንዘብ እርዳታ ያደርጋል፡፡
ቃል አቀባዩ ማሻሻያዎች ገቢራዊ መደረጋቸውን እስከምናረጋግጥ ድረስ ለኡጋንዳ ምንም አይነት የፋይናንስ ድጋፍ እቅድ ለቦርዱ አናቀርብም ብለዋል፡፡
ማሻሻያዎቹ ባንኩ ድጋፍ በሚያደርግባቸው ፕሮጀክቶች ላይ በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ላይ ምንም አይነት አድሎ ሳይደርስባቸው እንዲገለገሉ መፍቀድ አለባቸው ተብሏል፡፡
የምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ዋነኛ አበዳሪ ተቋም የሆነው የአለም ባንክ ሀገሪቱ ባሳለፍነው አመት ከተመሳሳይ ጾታ ግንኝኑነት ጋር በተያያዘ ያወጣችውን ህግ መነሻ በማድረግ የሚያደርገውን ድጋፍ አቋርጦ ነበር፡፡
የመንገድ መሰረተ ልማቶች እና በሀይል ማመንጫ ፕሮጄክቶች ላይ ከፍተኛ ገንዘብ ሲሰጥ የነበረው እርዳታ መቋረጡ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ ተነግሯል፡፡
በ2023 ግንቦት ወር ላይ የኡጋንዳ መንግስት ባወጣው የጸረ ተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ህግ ድርጊቱን ሲፈጸም የተገኘ ወይም እራሱን በዚህ መንገድ የገለጸ ሰው ከእድሜ ልክ እስራት እስከ ሞት ቅጣት የሚያስበይን ወንጀል ሆኗል፡፡
ህጉ መውጣቱን ተከትሎ አሜሪካ እና ምዕራባውያን በሀገሪቱ ላይ የተለያዩ ማእቀቦችን ሲጥሉ የአለም ባንክ በበኩሉ የምከተለውን እሴት የጣሰ ነው በሚል ለሀገሪቱ ገንዘብ ድጋፍ እንደማያደርግ አስታውቆ ነበር፡፡
ባንኩ ከሀገሪቷ ጋር እያደረኩት ነው ባለው ድርድር ምን አይነት ተጨማሪ ዝርዝር ማሻሻዎችን እንደሚፈልግ ግልጽ ባያደርግም ድርድሩ የሚሳካ ከሆነ ያቋረጠውንድጋፍ እንደሚያስቀጥል መናገሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡