እስራኤል ጋዛን ይዞ የመቆየት ፍላጎት እንደሌላት ገለጸች
እስራኤል እያደረሰች ባለው መጠነሰፊ ጥቃት በጋዛ ከ10ሺ በላይ ንጹሃን መገደላቸውን የፍልስጤም ባለስልጣናት ገልጸዋል
የእስራል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ እስራኤል ሀማስን ካሸነፈች በኋላ ጋዛን የመውር፣ የማስገበር ወይም የማስተደዳር እቅድ እንደሌላት ተናግረዋል
እስራኤል ጋዛን ይዞ የመቆየት ፍላጎት እንደሌላት ገለጸች።
የእስራል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ እስራኤል ሀማስን ካሸነፈች በኋላ ጋዛን የመውር፣ የማስገበር ወይም የማስተደዳር እቅድ እንደሌላት ተናግረዋል። ነገርግን በፍልስጤማ ግዛት ሌላ ታጣቂ ብቅ እንዳይል "ተአማኒ የሆነ ኃይል" መግባት ይኖርባታል ብለዋል ኔታንያሁ።
ኔታንያሁ በዚህ ሳምንት እስራኤል የጋዛን ደህንነት ላልተወሰነ ጊዜ መቆጣጠር እንደምትፈልግ ፍንጭ የሚሰጥ አስተያየት ሰጥተው የነበረ ሲሆን ይህም በአጋሯ አሜሪካ ጭምር አልተወደደላትም።
አሜሪካ እስራኤል ሀማስን ለማጥፋት እየደበደበቻት ያለችውን ጋዛ ወርራ የምትቆይ ከሆነ እንደምትቃወም ገልጻለች።
ኔታንያሁ ከአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ፎክስ ኒውስ ጋር በትናንትናው እለት በሰጡት ቃለ ምልልስ እስራኤል ኮጦርነቱ በኋላ "ጋዛን ማስገበር፣ መውረር እና ማስተዳደር አንፈልግም" ብለዋል።
በጋዛ የሲቪል አስተዳደር እንዲቋቋም ይደረጋል ያሉት ኔታንያሁ ይህ የሚሆነው ግን እስራኤል እንደ ጥቅምቱ አይነት ጥቃት የማይደገም መሆኑን ስታረጋግጥ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
"ስለዚህ በጋዛ ታማኝ ኃይል ኖሮ፣ አስፈላጊ ሲሆን ገዳዮችን ገብተን የምንገድልበት ሁኔታ መኖር አለበት። ምክንያቱም በዚህ መንገድ ነው የሀማስ አይነት ታጣቂ እንዳይፈጠር የምንከላከለው" ብለዋል ኔታንያሁ።
እስራኤል እያደረሰች ባለው መጠነሰፊ ጥቃት በጋዛ ከ10ሺ በላይ ንጹሃን መገደላቸውን የፍልስጤም ባለስልጣናት ገልጸዋል።
አለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እና በርካታ ሀገራት እስራኤል በጋዛ ተኩስ እንድታቆም ቢጠይቁም፣ እስራኤል እና አጋሯ አሜሪካ የተኩስ አቁሙን ሀሳብ አይቀበሉትም።
ተኩስ ማቆም የማይታሰብ መሆኑን የምትገልጸው እስራኤል እርዳታ እንዲደርስ ለማድረግ ግን ለሰአታት ጦርነቱን ጋብ ለማድረግ መስማማቷ ተነግሯል።