እስራኤል የፍልስጤም ታጣቂዎች ስድስት ሮኬቶችን ተኩሰውብኛል አለች
የእስራኤል ጦር አምስቱን ሮኬቶች በአየር መቃወሚያ መምታቱንና አንዱ ሰዎች በሌሉበት ሜዳማ ስፍራ መውደቁን ገልጿል
ለሮኬት ጥቃቱ የፍልስጤም ታጣቂዎች እስካሁን ሃላፊነቱን ባይወስዱም፥ ትናንት በናብሉስ ከተማ እስራኤል ለፈጸመችው የንጹሃን ግድያ ምላሽ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል
የፍልስጤም ታጣቂዎች ከጋዛ ሰርጥ ወደ ደቡባዊ እስራኤል ስድስት ሮኬቶችን ማስወንጨፋቸውን እስራኤል አስታወቀች።
የፍልስጤም ታጣቂዎች ግን ለዛሬ ማለዳው የሮኬት ጥቃት ሃላፊነት እንደሚወስዱ እስካሁን አልገለጹም።
እስራኤል ትናንት ጠዋት በናብሉስ አራት ስአት የወሰደ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍታ 11 ፍስጤማውያን መገደላቸው ተነግሯል።
የእስራኤል ወታደሮች የታጣቂዎች ዋነኛ ይዞታ ናት በምትባለው የገበያ ከተማ ናብሉስ የተደበቁ ታጣቂዎችን ለመያዝ ባደረጉት ጥረት በርካታ ንጹሃን መቁሰላቸውም ነው የተገለጸው።
ከታጣቂዎች ጋር ከተደረገው የተኩስ ልውውጥ ለማምለጥ የሚሞክሩ ንጹሃን በወታደሮች ተተኩሶባቸው ህይወታቸው ሲያልፍ የሚያሳዩ ምስሎችም ወጥተዋል።
በዚህም የፍልስጤሙ ሃማስ እና እንደ ኢስላሚክ ጂሃድ ያሉ ቡድኖች አጻፋውን እንደሚመልሱ መዛታቸውን ነው አሶሼትድ ፕረስ ያስታወሰው።
ዛሬ ማለዳ ወደ አሽኬሎን እና ስዴሮት ከተሞች የተተኮሱት አምስት ሮኬቶችም በታጣቂዎቹ ስለመፈጸማቸው ማረጋገጫ ባይሰጥም በእስራኤል ጦር አየር ላይ መመታታቸው ተገልጿል።
አንደኛው ሚሳኤልም ሰዎች በማይኖሩበት ሜዳማ ስፍራ መውደቁን ነው የእስራኤል ጦር ያስታወቀው።
የእስራኤል ፖሊስ የትናንቱን ጥቃት ተከትሎ በዌስትባንክ እኛ ምስራቅ እየሩሳሌም ነውጥ ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል በተጠንቀቅ ዝግጁ እንዲሆን ታዟል።
የእስራኤልና ፍልስጤማውያን ግጭት በተለይ ቤንያሚን ኔታንያሁ ዳግም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተመረጡ በኋላ ተባብሶ ቀጥሏል።
እስራኤል ግጭቱን ለማርገብ የሰፈራ ፕሮግራሙን ለማቋረጥ መስማማቷን በገለጸች በሶስተኛው ቀን በዌስትባንክ ከ2 ሺህ በላይ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችላትን እቅድ ዛሬ ይፋ ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእስራኤልን የሰፈራ ፕሮግራም አጥብቆ በተቃወመ ማግስት ይፋ ይደረጋል የተባለው እቅድ ግጭቱን እንዳያባብሰው ተሰግቷል።
በመንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤም አምባሳደር ሪያድ ማንሱር፥ አለም አቀፉ ማህበረሰብ በፍልስጤማውያን ላይ የሚፈጸም ጭፍጨፋን እንዲያስቆም ጠይቀዋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በበኩላቸው፥ “የእስራኤልን የደህንነት ስጋት እንጋራለን፤ ነገር ግን በሚወሰዱት እርምጃዎች እየጠፋ ያለው የሰው ህይወትም እጅግ አሳሳቢ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የአሶሼትድ ፕረስ ዘገባ እንደሚያሳየው የፈረንጆቹ 2023 ከገባ ወዲህ 60 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን በዌስትባንክና በእየሩሳሌም ተገድለዋል።