እስራኤል እና ፍልስጤም በመካከላቸው ያለውን ውጥረት እንዲያረግቡ አሜሪካ አሳሰበች
የእሰራኤል እና ፍልስጤም ፍጥጫ እንዲረግብ የሀገራት መሪዎች ጥሪያቸውን ማቅረባቸውን ቀጥለዋል
የዋሽንግተኑ ከፍተኛ ዲፕሎማት ብሊንከን የካይሮ ጉብኝታቸው አጠናቀው ወደ እስራኤልና ፍልስጤም አቅንተዋል
ከሰሞኑ ፍልስጤማውያን ባደረሱት ጥቃት ዜጎቼ ተገድለዋል የምትለው እስራኤል ተጨማሪ ወታደሮቿን በዌስት ባንክ ማሰማራቷንና እርምጃ መውሰድ መጀመሯን ተከትሎ በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል፡፡
እስራኤል በዚህ ወር ብቻ በዌስት ባንክ በሰነዘረቸው ጥቃት 35 ፍልስጤማውያን መገዳላቸውንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የሀገሪቱን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ሁኔታው ያስጨነቃትና በመካከለኛው ምስራቅ ዲፕሎማሲ ግንባር ቀደም ሚና ያላት አሜሪካም ታዲያ ሀገራቱ ውጥረቱን ከማባበስ እንዲቆጠቡ ጠይቃለች፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንክን ከሳኡዲው የቴሌቭዥን ጣቢያ አል አረቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ፤ እስራኤል እና ፍልስጤም በመካከላቸው ያለውን ውጥረት እንዲያረግቡ አሳስበዋል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ያሉት ብሊንከን ካይሮ ውስጥ በሰጡት መግለጫ፤ ሁሉም አካላት ነገሩን እንዲያረጋጉ እና ውጥረቱን እንዳያባብሱ መጠንቀቅ አለባቸው ብለዋል፡፡
"ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ እኛ የምናወግዛቸው እና የምንጸየፋቸው ዘግናኝ የሽብር ጥቃቶች አይተናል” ያሉት ከፍተኛ ዲፕሎማቱ፤ “የሁለት መንግስታት መፍትሄ ለማግኘት መስራት ያለውን ጠቀሜታ”ም አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የዋሽንግተን ከፍተኛ ዲፕሎማት አንቶኒ ብሊንከን ከፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ እና ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ጋር ከተገናኙ በኋላ ግብጽን ለቀው ወደ እስራኤል እና የፍልስጤም ግዛቶች ማምራታቸው ታውቋል፡፡
ብሊንከን በቀጣይ ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ከፍልስጤም መሪ ማህሙድ አባስ ጋር ይነጋገራሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡
በተያያዘ የእስራኤልና እና ፍልስጤም ፍጥጫ እንዲረግብ የሀገራት መሪዎች ጥሪያቸውን ማቅረባቸውን ቀጥለዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሁሉም ወገኖች ከተለመደው “የመጠቃቃት አዙሪት” እንዲወጡ ሲያሳስቡ የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው ሁሉም ወገኖች “ከፍተኛ ኃላፊነት” እንዲሰማቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይ ውጥረቱ ያሳሰባቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲስ እየሆነ ባለው ነገር (የሰዎች ሞት) ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡