አረብ ኤምሬትስ የሚመራና በ9 ዓመታት ውስጥ የእስራኤልን ሰፈራ የሚያወግዝ የመጀመሪያው የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ አለፈ
አቡዳቢ ውሳኔውን የፍልስጤማውያን መብት የሚደግፍ የመጀመሪያው ነው ብላዋለች
እስራኤል የጸጥታው ምክር ቤት መግለጫን በመኮነን አልቀበለውም ብላለች
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የእስራኤልን ሰፈራ የሚያወግዝ ውሳኔ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ አሳልፏል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት የዲፕሎማሲ አማካሪ ዶ/ር አንዋር ጋራካሽ ውሳኔው የፍልስጤማውያን መብት የሚደግፍ የመጀመሪያው ነው ብለዋል።
አማካሪው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለፍልስጤም ጉዳይ ገንቢ እርምጃ በመውሰዷ የሀገሪቱ ዲፕሎማሲ አወንታዊ አመራር ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
የጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንታዊ መግለጫ የእስራኤልን ግንባታና መስፋፋት በአንድ ድምጽ አውግዟል።
የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት እስራኤል በፍልስጤም ውስጥ ሰፈራዋን ለማስፋፋት ባቀደችው እቅድ የተሰማውን ጥልቅ ስጋትና ቁጣ ገልጿል።
ኃያላን አባላቱ "ሰላምን የሚያደናቅፍ የአንድ ወገን እርምጃዎችን አጥብቀን እንቃወማለን" ብለዋል።
እርምጃዎቹም "የእስራኤል ግንባታና የሰፈራ መስፋፋት፣ የፍልስጤምን መሬቶች መውረስ፣ በውጭ መከላከያ ኃይልን ህጋዊ ማድረግ፣ የፍልስጤም ቤቶችን ማፍረስ እና የፍልስጤም ሰላማዊ ዜጎች ማፈናቀል" ናቸው ተብሏል።
በመግለጫው የ15ቱ የምክር ቤቱ አባል ሀገራት "እስራኤልና ፍልስጤም በአስተማማኝና በተለዩ ድንበሮች ውስጥ በሰላም አብረው የሚኖሩበት የሁለት ሀገር የመፍትሄ ሀሳብ ላይ ለመድረስ የማያወላውል ቁርጠኝነት" እንዳላቸው አረጋግጧል።
ባለፈው ሰኞ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በዚህ ጉዳይ ላይ አስገዳጅ ውሳኔ እንዲሰጥ ሃሳብ ያቀረበች ሲሆን ምክር ቤቱም የጋራ መግለጫ አውጥቷል።
አሜሪካ ለአስርት ዓመታት የእስራኤልን የሰፈራ እንቅስቃሴ በአብዛኛው በመተቸትና እና ለሰላም ጥረቶች እንቅፋት መሆኑን በመግለጽ ትታወቃለች።
ሆኖም ዋሽንግተን አብዛኛውን ጊዜ ሰፈራውን "ህገ-ወጥ" በማለት በይፋ መግለጽ አትፈልግም ነበር ተብሏል።
ሀገሪቱ ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ከእስራኤል ጋር የተያያዙ ወሳኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውሳኔዎችን ድምጽን በድምጽ በመሻር ውድቅ አድርጋለችም።
እስራኤል የጸጥታው ምክር ቤት መግለጫን ኮንናለች።
በተለይም የቅርብ ወዳጇና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል በሆነችው ዋሽንግተን ደስተኛ አለመሆኗ ተዘግቧል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት “ይህ የአንድ ወገን መግለጫ በፍጹም መደረግ አልነበረበትም። አሜሪካም መቀላቀል አልነበረባትም” ብሏል።
ባለፈው ሳምንት የእስራኤል መንግስት በፍልስጤማውያን የደረሱ ሁለት ጥቃቶችን ተከትሎ በዌስት ባንክ የሚገኙ ዘጠኝ ሰፈራዎችን እንደገና ህጋዊ እንደሚያደርግ አስታውቋል።