ኢትዮጵያ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በፍልስጤም ጉዳይ ባሳለፈው ውሳኔ ምን አቋም ያዘች?
የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በፍልስጤም የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በ124 ድጋፍና በ14 ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል
ውሳኔውን የፍልስጤም አስተዳደር “ታሪካዊ”፤ እስራኤል ደግሞ “ሽብርተኝነትን መደገፍ” ነው ብለውታል
የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እስራኤል በጋዛ እና ዌስትባንክ የምታደርገውን “ህገወጥ ወረራ” እንድታቆም በፍልስጤም አስተዳደር የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ አጸደቀ።
193 አባላት ያለው ጠቅላላ ጉባኤ በ124 ድጋፍ፣ በ14 ተቃውሞና በ43 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።
የውሳኔ ሃሳቡ ሁሉም የእስራኤል ወታደሮችና በሃይል በተቆጣጠረቻቸው አካባቢዎች የሰፈሩ እስራኤላውያን በ12 ወራት ውስጥ እንዲወጡ የሚጠይቅ ነው።
ቴል አቪቭ በህገወጥ ወረራው ጉዳት ለደረሰባቸው ፍልስጤማውያን ካሳ እንድትከፍልም ይጠይቃል።
የውሳኔ ሃሳቡ ሀገራት በፍልስጤም “ህገወጥ ወረራ” የሚፈጽሙ አካላት ላይ ማዕቀብ እንዲጥሉና ለእስራኤል የጦር መሳሪያ መሸጥ እንዲያቆሙም ጥሪ ያቀርባል።
የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ “የውሳኔ ሃሳቡ መጽደቅ ነጻ ሀገር መመስረት ለሚሹትና በጋዛና ዌስትባንክ ለሚጨፈጨፉት ፍልስጤማውያን ተስፋ ነው፤ አለማቀፉ ማህበረሰብ እስራኤል ለውሳኔ ተገዥ እንድትሆን ጫና ሊያደርጉባት ይገባል” ብለዋል።
በመንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤም አምባሳደር ሪያድ መንሱርም ውሳኔው “የእስራኤል ወረራ በአስቸኳይ ቆሞ የፍልስጤማውያን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት መከበር እንዳለበት ግልጽ መልዕክት ያስተላለፈ ነው” ማለታቸውን ዩሮ ኒውስ አስነብቧል።
በተመድ የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን በበኩላቸው፥ “አሳፋሪው ውሳኔ ለፍልስጤም አስተዳደር የዲፕሎማሲያዊ ሽብር ድጋፍ የሰጠ ነው” በሚል ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ አስገዳጅነት ባይኖረውም አለማቀፉ ማህበረሰብ ለፍልስጤማውያን ድምጽ እየሆነ መምጣቱን ያመላክታል ተብሏል።
ጠቅላላ ጉባኤው በትናንትናው እለት ያጸደቀው የውሳኔ ሃሳብ አለማቀፉ ፍርድቤት (አይሲጄ) በሀምሌ ወር ያሳለፈውን ውሳኔ የሚደግፍ ነው።
ፍርድቤቱ እስራኤል በፍልስጤም ግዛቶች ላይ “ወረራ መፈጸሟ ህገወጥ ነው”፤ በዌስትባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም የምታካሂደው የሰፈራ ፕሮግራምም ሊቆም ይገባል የሚል ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ትናንት ፍልስጤም ባቀረበችው የውሳኔ ሃሳብ ድምጽ ሲሰጥ የእስራኤል አጋር አሜሪካ ተቃውሟቸውን ካሰሙ 14 ሀገራት መካከል አንዷ ሆናለች።
የዋሽንግተን አጋሮች ፈረንሳይ፣ ፊንላንድ እና ሜክሲኮ ግን የውሳኔ ሃሳቡን የደገፉ ሲሆን፥ ብሪታንያ፣ ዩክሬን እና ካናዳ ድምጽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ኢትዮጵያም በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ድምጽ ለመስጠት ከታቀቡ 43 ሀገራት መካከል ተካታለች።