እስራኤል፤ ከቱርክ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ እንደምትመልስ አስታወቀች
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር፤ የግንኙነቱ እንደገና መጀመር “ለዜጎቻችን በጣም ጠቃሚ የኢኮኖሚ ዜና ነው” ብለዋል
ግንኙነቱን በማደስ ውሳኔ ዙሪያ የእስራኤሉ መሪ ላፒድ ከቱርኩ አቻቸው ኤርዶጋን ጋር በስልክ ተወያይተዋል
እስራኤል ከቱርክ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ለመመለስ መወሰኗን አስታወቀች።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፤ ለሁለትዮሽ ጥቅም ሲባል በሀገራቱ መካከል የነበረውን መልካም የሚባል ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ያየር ላፒድ የሚመሩት መንግስት መወሰኑን አስታውቋል።
በሀገራቱ መካካል የነበረው ግንኙነት ለማደስ ከውሳኔ የተደረሰው፤ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ያየር ላፒድ እና የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን የስልክ ውይይት ካደረጉ በኋላ መሆኑም ታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ያየር ላፒድ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ “እስራኤል እና ቱርክ አምባሳደሮቻቸው እየመለሱ ነው” ብለዋል።
ላፒድ፤ ከቱርክ ጋር ያለው ግንኙነት እንደገና መጀመሩ የቀጠናዊ መረጋጋትን ከማጠናከር በዘለለ “ለዜጎቻችን በጣም ጠቃሚ የኢኮኖሚ ዜና ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ በበኩላቸው፤ ከቱርክ ጋር የተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት "ጠቃሚ እርምጃ" ሲሉ አድንቀዋል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ፤ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ባለፉት ወራት እድገት የታየበት ሲሆን፤ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት የጉብኝት ልውውጥ አድርገዋል።
ላፒድ በሰኔ ወር2022 አንካራ በጎበኙበት ወቅት ከፕሬዝዳንት ኤርዶጋን እና ሌሎች የሀገሪቱ ባለስልጣናት ስምምነት የተደረሰባቸው ቁልፍ ጉዳዮች መልካም የሚባሉ ውጤቶች ማሳየታቸው አሁን ለተደረሰው ውሳኔ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለውም ይታመናል።
እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ መሆኗን እውቅና መስጠቷንና በ2010 በሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ በእስራኤል የባህር ኃይል እና እስራኤል በሃማስ ቁጥጥር ስር በሚገኘው የጋዛ ሰርጥ ላይ የጣለችውን እገዳ ለመስበር በሞከረው በቱርክ ፍሎቲላ (ፍሪ ጋዛ ሙቭመንት የተኘ እንቅስቀሴ የሚያራምደው ኃይል) መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ግንኙነታቸው ሻክሮ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
በዚህም የተነሳ ሁለቱም ሀገራት እንደፈረንጆቹ 2017 ምባሳደሮቻቸውን ማንሳታቸው አይዘነጋም።