እስራኤል በራፋህ ዘመቻ የአሜሪካን ቀይ መስመር አላለፈችም - ዋይትሃውስ
የእስራኤል ጦር በራፋህ መሃል ደርሶ የአየር ጥቃቱም የንጹሃንን ህይወት መቅጠፉን በቀጠለበት ወቅት ነው አሜሪካ ይህን ያለች
እስራኤል በምስራቃዊ ራፋህ የጀመረችውን ዘመቻ ወደ ማዕከላዊና ሰሜናዊ የከተማዋ ክፍል አስፋፍታለች
እስራኤል በራፋህ እያካሄደችው ያለው ዘመቻ የአሜሪካን ቀይ መስመር አለማለፉን የዋይትሃውስ ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ገለጹ።
ቃል አቀባዩ ይህን ያሉት የእስራኤል ጦር በራፋህ መሃል መድረሱና ከግብጽ ጋር በሚያዋስነው ድንበር ዙሪያ ስትራቴጂካዊ ፋይዳው ከፍ ያለን ተራራ መቆጣጠሩ ከተገለጸ ከስአታት በኋላ ነው።
እስራኤል ከ23 ቀናት በፊት በምስራቃዊ ራፋህ የጀመረችውን ዘመቻ ወደ ማዕከላዊና ሰሜናዊ የከተማዋ ክፍል ማስፋፋቷንና በአየር ጥቃት የሚቀጠፈው የንጹሃን ህይወት እየጨመረ ቢሄድም አሜሪካ እስካሁን ቀይ መስመሩ አልታለፈም ብላለች።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዚህ ወር መጀመሪያ እስራኤል በራፋህ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በተጠለሉባቸው መኖሪያ መንደሮች ከገባች የጦር መሳሪያ አቅርቦታችን እናቋርጣለን ማለታቸው ይታወሳል።
የዋይትሃውስ ቃልአቀባይ ጆን ኪርቢ እስራኤል በአሜሪካ የተቀመጠውን ገደብ ጥሳ ጥቃት እየፈጸመች አይደለም ወይ በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ፥ “የእስራኤል ጦር በብዛት ወደ ራፋህ ሲገባ አላየንም፤ በተጠና ሁኔታ ኢላማዎችን ለይቶ እየመታ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከ45 በላይ ፍልስጤማውያን የተገደሉበትን የእስራኤል የአየር ጥቃት “ልብ የሚሰብር” ከማለት ውጪም አሜሪካ በራፋህ ጉዳይ ያስቀመጠችው ቀይ መስመር ስለመጣሱ አልጠቀሱም።
የራፋሁ ዘመቻ የጋዛን ቀውስ ያባብሳል በሚል ከአለማቀፉ ማህበረሰብ የቀረቡ ጥሪዎችን ሁሉ ያልተቀበለው የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደር በዘመቻው ገፍቶበታል።
የመንግስታቱ ድርጅት 1 ሚሊየን የሚጠጉ በራፋህ ተጠልለው የቆዩ ፍልስጤማውያን ከከተማዋ መውጣታቸውንና አሁንም ድረስ በመቶ ሺዎች የሚቆጥሩ ሰዎች ህይወት አደጋ ውስጥ መሆኑን ገልጿል።
የጋዛው ጦርነት በድል የሚጠናቀቀው በራፋህ የመሸጉ የሃማስ ታጣቂዎችን ሲደመሰሱ ነው ያለችው ቴል አቪቭ፥ አል አውዳ የተባለውን የራፋህ አማካይ ስፍራ መቆጣጠሯን ቢቢሲ የአይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።
በተመድ የፍልስጤም የእርዳታ ድርጅት ቃል አቀባዩ ሳም ሮስም በራፋህ እንደሚገኙና ባለፉት ቀናት ጦርነቱ እየተስፋፋ ወደ ምዕራባዊ የከተማዋ ክፍል እየተጠጋ መሆኑን ነው የገለጹት።
የእስራኤል ታንኮች በአል ማዋሲ በድንኳን በተጠለሉ ፍልስጤማውያን ላይ ጥቃት አድርሰው በጥቂቱ 21 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያሳያል።
ስምንተኛ ወሩን ሊይዝ በተቃረበው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ፍልስጤማውያን ቁጥር 36 ሺህ 90 ደርሷል፤ የእስራኤል የራፋህ ዘመቻም በየቀኑ ንጹሃንን መቅጠፉን ቀጥሏል።