ደማስቆን የተቆጣጠረው የሶሪያ አማጺ ቡድን በመጀመሪያ የቴሌቭዥን መግለጫው ምን አለ?
9 ሰዎችን የያዘ የአማጺው ቡድን በሶሪያ ብሄራዊ ቴሌዝቭን ስቱዲዮ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል

በመግለጫውም ሶሪያን ለ24 ዓመታ የገዙት ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ከስልጣን መወገዳቸውን አረጋግጠዋል
የሶሪያዋ ዋና ከተማ ደማስቆን የተቆጣጠረው የሶሪያ አማጺ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌቭዥን ቀርቦ በሰጠው መግለጫ “በሽር አል አሳድን ከስልጣን አውርደናል” አለ።
የሶሪያ አማጽያ ቡድን በዛሬው እለት የሀገሪቱ መዲና ደማስቆን መቆጣጠሩን ተከትሎ ዘጠኝ ሰዎችን የያዘ ቡድን በሶሪያ ብሄራዊ ቴሌዝቭን ስቱዲዮ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆ በአማጽያኑ እጅ መውደቋን እና ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ከስልጣን መወገዳቸውን አረጋግጧል።
“በእስር ቤት የሚገኙ እስረኞች በሙሉ ተፈትተዋል” ያለው አማጺ ቡድኑ እስረኞቹን “የተጨቆኑ” በማለት ገልጿቸዋል።
አማጺ ቡድኑ ቃል አቀባይ ታጣቂዎች እና ነዋሪዎች ወደ ሀገሪቱ ህዝባዊ ተቋማት እንዳይቀርቡ እና ተቋማቱን ከማንኛውም ጥቃት እንዲጠብቁም ጠይቀዋል።
ለ24 ዓመታት የዘለቀው የበሽር አል አሳድ አገዛዝ ማብቃቱን የሶሪያ ጦር አዛዥ ለሀገሪቱ ጦር አመራሮች ማሳወቃቸው ሮይተረስ ምንጮች ጠቅሶ መዘገቡ ይታወቃል።
ሶሪያን ለ24 ዓመታት የገዙት ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ዛሬ ማለዳ ላይ አውሮፕላን ተሳፍረው ስፍራው ለጊዜው ወዳልታወቀ ቦታ መኮብለላቸውም ነው የተገለጸው።
ከኢድሊብ የተነሳው ሃያት ታህሪር አል-ሻም አማጺ ቡድን ባለፉት ቀናት በአላሳድ ጦር ላይ በከፈተው ጥቃት፥ አሌፖ፣ ሃማ እና ሆምስ የተሰኙ ቁልፍ ከተሞችን መቆጣጠሩ ይታወሳል።
የአማጺ ቡድኑ ግስጋሴውን በመቀጠልም ነው በዛሬው እለት የሶሪያ ርዕሰ መዲናዋን ደማስቆ ከአላሳድ አገዛዝ ነጻ ማውጣቱን ያስታወቀው።
ይህንን ተከትሎም 53 ለሚያህሉ ዓመታት ዘልቆ የቆየው የአባትና ልጅ የአገዛዝ ዘመን ማብቃቱ ነው የተነገረው።
የፕሬዝዳንት በሽል አል አሳድ አባት የሆኑት ሃፌዝ አል አሳድ ሶሪያን ከፈረንጆቹ 1971 አስከ 2000 ድረስ በፕሬዝዳትነት መርተዋል።
ልጃቸው በሽር አላሳድ ደግሞ ከ2000 ጀምሮ ሀገሪቱን በፕሬዝዳንትነት እየመሩ ዘልቀዋል።