የኃያላኑ ሀገራት የሃይፐርሶኒክ ሚሳይል ልማት ፉክክር
የባለስቲክ ሚሳይል ጥቃትን መመከት የሚያስችል አቅም አልገነባችም የተባለችው አሜሪካም በ2023 ትልቁ ትኩርቷ ይሄው እንደሚሆን ይጠበቃል
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን አዳዲስ አህጉር አቋራጭ ሃይፐርሶኒክ የባለስቲክ ሚሳኤሎች እንዲለሙ አዝዘዋል።
ሚሳይሎቹ ፒዮንግያንግ ሊፈጸምባት ለሚችል የኒዩክሌር ጥቃት አጻፋውን መመለስ ያስችላታል ተብሏል።
በትናትናው እለት አጭር ርቀት ተምዘግዛጊ የባለስቲክክ ሚሳይል ወደ ጃፓን ባህር ያስወነጨፈችው ሰሜን ኮሪያ፣ አሜሪካ ሊደርሱ የሚችሉ አህጉር አቋራጭ የባለስቲክ ሚሳኤሎች ያስፈልጉኛል ብላለች።
የሃይፐርሶኒክ ባለስቲክ ሚሳይሎች ከድምጽ ፍጥነት በአምስት እጥፍ ፈጣን መሆናቸው ይነገራል ፤ በስአት ከ6 ሺህ 100 ኪሎሜትሮች በላይ ይምዘገዘጋሉ።
ከመሬት ወደ ሰማይ ተወንጭፈው ወደ ኢላማቸው የሚመለሱበት ፍጥነትም አስደናቂ ነው።
ይህም ከራዳር እይታ ውጭ እንዲሆኑና ተመተው እንዳይወድቁ አድርጓቸዋል ነው የሚሉት ባለሙያዎች።
የአሜሪካው ናሽናል ኢንተረስት ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ ብቻ ሳይሆን ከሩስያ እና ቻይና በኩል እየተደረገ ያለው ዝግጅት እያሳሰባት ይገኛል ይላል።
ጋዜጣው ሩስያ የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎቿን ከአየር ላይ (ኪንዛሃል) እንዲሁም በባህር ውስጥ (ዚርኮርን) እየሞከረች ነው።
ኪንዛሃል የተሰኘውን ሚሳኤልም በመጋቢት ወር 2022 በዩክሬን መሞክሯን ያወሳል።
ቻይናም ሃይፐርሶኒክ ክሩዝ ሚሳኤሎችን በ2021 መሞክሯን ነው ናሽናል ኢንተረስት ያስነበበው።
አሜሪካ ግን የመጀመሪያ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሏን በቅርቡ የሞከረችው በታህሳስ 12 2022 መሆኑን የሚጠቅሰው ዘገባው፥ ዋሽንግተን የሃይፐርሶኒክ ባለስቲክ ሚሳኤል ልማት ላይ ብቻ ሳይሆን መከላከሉ ላይም ልትሰራ እንደሚገባ ይጠቁማል።
የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች በተወነጨፉበት ቅጽበት የሚያሳውቁ የህዋ ላይ ሴንሰሮች በስፋት እንዲገጠሙም የባለሙያዎችን ምክረ ሃሳብ ያክላል ዘገባው።
ሰሜን ኮሪያም ሆነች ሩስያ አህጉር አቋራጭ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን ቢያስወነጭፉ አሜሪካ ልታስቆመው አትችልም የሚለው ጋዜጣው የተቀናቃኞቿ አካሄድ ሊያሳስባት እንደሚገባ ያሳስባል።
የአሜሪካ አየር ሃይል የባለስቲክ ሚሳኤሎችን ለመሞከር ራይቲዮን ሚሳኤልስ ኤንድ ዲፌስ ከተባለ ተቋም ጋር የቢሊየን ዶላሮች ውል መፈረሙ ይታወሳል።
የሃዩፐርሶኒክ ፍጥነት ያላቸው ክሩዝ ሚሳኤሎችን በስፋት ለማምረት የሚያስችል ስምምነትም ሊዮዶስ ከተባለ ተቋም ጋር መፈራረሙ ነው የተነገረው።
ይህ ሁሉ በቂ አለመሆኑን የሚያነሳው ናሽናል ኢንተረስት ጋዜጣ ግን የባይደን አስተዳደር የ2023 ትኩረቱ የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ጉዳይ እንዲሆን ያሳስባል።
በ2022 ከ70 በላይ ሚሳኤሎችን የሞከረችው ሰሜን ኮሪያ የሃይፐርሶኒክ የባለስቲክ ሚሳኤል ፉክክሩን ትመራለች፤ በዩክሬኑ ጦርነት እና በታይዋን ጉዳይ ከአሜሪካ ጋር የተፋጠጡት ሩስያ እና ቻይናም ኒዩክሌር የሚሸከሙ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን መሞከራቸውን ገፍተውበታል።
ፒዮንግያንግ በ2023ትም አህጉር አቋራጭ የባለስቲክ ሚሳኤል በስፋት ይሰራ ማለቷ ውጥረቱን አባብሶታል።