እስራኤል በሊባኖስ በፈጸመችው የአየር ጥቃት 60 ሰዎች መገደላቸው ተነገረ
በሊባኖስ ምስራቃዊ ክፍል ባካ በተባለው አካባቢ በተፈጸመው ጥቃት ከ58 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውንም የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ገልጿል
ጥቃት የተፈጸመበት የባካ ሸለቆ የሄዝቦላህ ዋነኛ ምሽግ እንደሆነ ይነገራል
እስራኤል በምስራቃዊ ሊባኖስ በፈጸመችው ጥቃት በጥቂቱ የ60 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነገረ።
ባካ በተሰኘው ሸለቋማ ስፍራ በተፈጸመው ጥቃት ከሞቱት ውስጥ ሁለት ህጻናት እንደሚገኙበት የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ባልቤክ በተባለው ግዛት ውስጥ በሚገኙ 16 አካባቢዎች የአየር ድብደባ መፈጸሙን የገለጸው ሚኒስቴሩ፥ በጥቃቶቹ ከ58 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውንም ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።
የባልቤክ ግዛት አስተዳዳሪ ባቼ ሆድር በአል አላቅ ከተማ 16 የአንድ ቤተሰብ አባላት መገደላቸውን በመጥቀስ የነፍስ አድን ስራዎች መቀጠላቸውን ተናግረዋል።
በማህበራዊ ሚዲያዎች የተጋሩ ትክክለኛነታቸው ያልተረጋገጠ ምስሎች በእሳት የተያያዘ ጫካ እና የተጎዱ ህንጻዎችን አሳይተዋል ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።
ጥቃት የተፈጸመበት የባካ ሸለቆ የሄዝቦላህ ተዋጊዎች የመሸጉበት እንደሆነ ይነገራል።
ባለፉት አምስት ቀናት በሄዝቦላህ ይዞታዎች ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የአየር ድብደባዎችን የፈጸመው የእስራኤል ጦር በጥቂቱ 60 ሰዎች ለተገደሉበት ጥቃት እስካሁን ማብራሪያ አልሰጠም።
በደቡባዊ ሊባኖስ ከእስራኤል ወታደሮች ጋር ውጊያ እያካሄደ የሚገኘው ሄዝቦላህ በትናንትናው እለት በእስራኤሏ የወደብ ከተማ ሃይፋ አቅራቢያ በሚገኝ የባህር ሃይል ጣቢያ ሮኬቶችን መተኮቹን ገልጿል።
እስራኤልና ሄዝቦላህ የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ የተኩስ ልውውጥ መጀመራቸው ይታወሳል።
ከአንድ ወር በፊት እስራኤል እግረኛ ጦሯን ወደ ሊባኖስ ካስገባች ወዲህም የእስራኤል የአየር ድብደባና የሄዝቦላህ የሮኬት ጥቃት ተባብሶ ቀጥሏል።
የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር ከ2 ሺህ 700 በላይ ሰዎች መገደላቸውና ከ12 ሺህ 400 በላይ መቁሰላቸውን አስታውቋል።
ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ሊባኖሳውያንን ያፈናቀለው የእስራኤልና ሄዝቦላህ ጦርነት እንዲቆም የተደረጉ ሙከራዎች እስካሁን ውጤት አላመጡም።