አሜሪካ በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ ዛሬ ልዑካኗን ወደ ቤሩት ትልካለች
እስራኤል ከሄዝቦላህ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ቅድመ ሁኔታዎቿን ለአሜሪካ መስጠቷ ተሰምቷል
የሊባኖስን የአየር ክልል በነጻነት መጠቀም የሚለው ከቅድመ ሁኔታዎቿ መካከል ተካቷል
በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የሚመክር የአሜሪካ ልኡክ በዛሬው እለት ወደ ቤሩት ያቀናል።
አዳሩን እስራኤል በሊባኖስ የምታደርገውን የአየር ጥቃት አጠናክራ ስትቀጥል፤ በአሜሪካ ልዩ ልኡክ አሞስ ሃክስታይን የሚመራ ቡድን በእስራኤል እና ሄዝቦላህ የተኩስ አቁም ሁኔታ በተመለከተ ከሊባኖስ ባለስልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ ሮይተርስ ዘግቧል።
እስራኤል በሊባኖስ ያለውን ጦርነት ለማስቆም ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ለመስጠት ቅድመ ሁኔታዎችን የያዘ ሰነድ ለአሜሪካ መስጠቷ ተሰምቷል።
በዚህ ሰነድ ውስጥ ሄዝቦላህ እንዳይታጠቅ ፣ ድጋሚ እንዳይደራጅ እና ወታደራዊ መሠረተ ልማቶችን በድንበር አቅራቢያ እንዳይገነባ የእስራኤል ጦር ወታደራዊ ዘመቻዎችን እንዲያከናውን እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
በተጨማሪም የአየር ሀይሏ የሊባኖስ አየር ክልልን ያለምንም ክልከላ በነጻነት እንዲጠቀም ጥያቄ አቅርባለች፡፡
ሊባኖስ እስራኤል ያቀረበችውን ቅድመ ሁኔታ ትቀበላለች ተብሎ እንደማይጠበቅ የአሜሪካ ባለስልጣናት መናገራቸውን የጠቀሰው ሮይተርስ በዚህ ሁኔታ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረስ እንኳን የጦርነቱን መጠን ይቀንሰዋል እንጂ የማያስቆመው እንደሆነ መናገራቸውን አስነብቧል፡፡
አሜሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ኃያላን በጋዛ ውስጥ የተኩስ አቁም ስምምነትን ለማረጋገጥ ለአንድ ዓመት ያህል የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደረጉም እስካሁን አልተሳካላቸውም ፡፡
በዚህ የተነሳም የሊባኖስ ዲፕሎማቶች አና ባለስልጣናት በተኩስ አቁም ስምምነቶች እምብዛም ተስፋ እንደሌላቸው ተገልጿል፡፡
የአሜሪካ ልኡክ አሞስ ሃክስታይን ከሊባኖስ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚንስትር ናጂብ ሚካቲ እንዲሁም በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መካከል የተኩስ አቁም ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ከሚገኙት ከፓርላማው አፈጉባኤ ናቢህ በሪ ጋር በዛሬው እለት ይገናኛሉ፡፡
ዲፕሎማቱ ከባለስልጣናቱ ጋር በሚኖራቸው ቆይታ እስራኤል ያቀረበቻቸውን ተቀባይነት ይኖራቸዋል ተብለው የማይጠበቁ ቅድመ ሁኔታዎችን እንደሚያቀርቡ እና እንደማያቀርቡ የታወቀ ነገር የለም፡፡
አፈጉባኤው በሪ የአሜሪካው ዲፕሎማት አሞስ ጉብኝት የአሜሪካ ምርጫ ከመከናወኑ በፊት የተኩስ አቁም ግቢራዊ ለማድረግ የመጨረሻ እድላችን ነው ብለዋል፡፡
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ እስራል በሊባኖስ እና በጋዛ የምታደርገውን ውግያ አጠናክራ ስትቀጥል የሚፈናቀሉ እና የሚሞቱ ንጹሀን ቁጥርም በዛው ልክ ስለማሻቀቡ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡
እሁድ አመሻሽ ላይ ከሄዝቦላህ ጋር ግንኑነት አላቸው የሚባሉ በቤካ ተራራማ አካባቢዎች የሚገኙ የገንዘብ ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈጽማለች፡፡
በእስካሁኑ ውግያ ከ2400 በላይ ሊባኖሳውያን ሲገደሉ 1.2 ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡