ቤሩት እንዴት አደረች? በደቡባዊ ሊባኖስ እየተካሄደ ያለው የእስራኤልና ሄዝቦላህ ጦርነትስ?
የእስራኤል ጦር በቤሩት በፈጸመው የሚሳኤል ጥቃት በጥቂቱ ስድስት ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል
እስራኤል ከሄዝቦላህ ጋር ጦርነት ከጀመረች ወዲህ ትናንት ከፍተኛውን የሞት መጠን አስመዝግባለች
እስራኤል በሊባኖስ መዲና ቤሩት በዛሬው እለት በፈጸመችው ጥቃት ስድስት ሰዎች መገደላቸው ተነገረ።
የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ በተገደለበት አካባቢ በሶስት ሚሳኤሎች የተፈጸመው ጥቃት ሰባት ሰዎችን ማቁሰሉንም የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በትናንትናው እለት በቤሩት ከደርዘን በላይ የአየር ጥቃቶችን የፈጸመው የእስራኤል ጦር በሄዝቦላህ ላይ የተጠና ጥቃት እንደሚፈጽም ቢገልጽም ንጹሃን እየሞቱ ነው ተብሏል።
የቴል አቪቭ የአየር ጥቃት ባለፉት 24 ስአት ብቻ 46 ሰዎችን መግደሉንም ነው የሊባኖስ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ሬውተርስ የዘገበው።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ አቪቻይ አድሬ ግን ጥቃቱ ስለሚቀጥል ከመኖሪያ መንደራቸው እንዲወጡ የተደረጉ ሊባኖሳውያን በቀጣይ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ ወደ ቤታቸው እንዳይመለሱ አሳስበዋል።
የቃል አቀባዩ አስተያየት በቤሩት የሚፈጸመው ድብደባ እንደሚቀጥልና እስራኤል በሊባኖስ የሄዝቦላህን ዋሻዎችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ለማፈራረስ “የተገደበ ዘመቻ” ነው በሚል የጀመረችው የእግረኛ ውጊያ አድማሱን እያሰፋ መሄዱ እንደማይቀር አመላክች መሆኑ ተገልጿል።
በደቡባዊ ሊባኖስ ከሄዝቦላህ ጋር ፊት ለፊት እየተዋጋች ያለችው እስራኤል በትናንትናው እለት ስምንት ወታደሮቿን አጥታለች፤ ይህም ከሄዝቦላህ ጋር የተኩስ ልውውጥ ማድረግ ከጀመሩበት ጥቅምት 2024 ወዲህ ከፍተኛው አሃዝ ነው ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሀዘናቸውን በገለጹበት የቪዲዮ መልዕኽት “እኛን ለማጥፋት ከሚያሴሩ የኢራን አንጃዎች ጋር ከባድ ውጊያ እያደረግን ነው፤ በጋራ ሆነን ማሸነፋችን አይቀርም” ብለዋል።
የእስራኤልን ወታደሮች ከሊባኖስ ድንበር ለማስወጣት የተዋጊም ሆነ የጦር መሳሪያ አቅሙ አለኝ ያለው ሄዝቦላህ፥ ሶስት የእስራኤል ታንኮችን ማሩን ኤል ራስ በተባለች ከተማ በሮኬት መትቶ ማውደሙን ገልጿል።
የእስራኤል ጦርም ተጨማሪ ወታደሮች እና ሜካናይዝድ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ እያስገባ መሆኑ ነው የተዘገበው።
የጋዛውን ጦርነት ተከትሎ የተቀሰቀሰው የእስራኤልና ሄዝቦላህ ግጭት ከ1 ሺህ 900 በላይ ሊባኖሳውያንን ህይወት ቀጥፎ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ዜጎችን አፈናቅሏል።