ሶሪያ በእስራኤል የአየር ድብደባ አራት ወታደሮቿ መገደላቸውን ገለፀች
በዩክሬኑ ጦርነት የሶሪያን ሰማይ ከምትቆጣጠረው ሩስያ ጋር የተኮራረፈችው እስራኤል ምንም ምላሽ አልሰጠችም
ባለፈው ሳምንትም በተመሳሳይ ሁለት ወታደሮች ለደገደሉበት ጥቃት ቴል አቪቭ እጇ እንዳለበት ተገልጿል
ማዕከላዊ ሶሪያ ዛሬ በእስራኤል የአየር ጥቃት መናጡን የሶሪያ ጦር ገልጿል።
በጥቃቱ አራት ወታደሮች መገደላቸውንም ነው የሀገሪቱ ብሄራዊ የዜና ወኪል ሳና ያስነበበው።
ስማቸው ያልተጠቀሰ የሶሪያ ወታደራዊ አዛዥ የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች በሜዲትራኒያን ሲያንዣብቡ ቆይተው ወደ ማዕከላዊ ሶሪያ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፋቸውን ተናግረዋል።
የሶሪያው የሰብአዊ መብቶች ተቆጣጣሪ ገለልተኛ ተቋምም የከፍተኛ ፍንዳታ ድምፅ ላታኪያ፣ ሃማ እና ሆምስ እስከተሰኙት ከተሞች ድረስ መሰማቱን ገልጿል። ይሁን እንጂ ተቋሙ ዝርዝር መረጃን አላወጣም።
ሶሪያ ባለፈው ሳምንትም ሁለት ወታደሮቿ ለተገደሉበትና ሶስት ለቆሰሉበት ጥቃት እስራኤልን ተጠያቂ ማድረጓ ይታወሳል።
የእስራኤል መከላከያ በበኩሉ የተለመደ ዝምታውን መርጧል።
የሀገሪቱ ጦር በሶሪያ ስለሚፈፀሙ የአየር ላይ ጥቃቶች አስተያየት ሲሰጥ አይደመጥም፤ ይሁን እንጂ በኢራን የሚደገፉ ናቸው የምትላቸው ሃይላት ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአየር ድብደባዎችን መፈፀሟን አትክድም።
እስራኤል ለሊባኖሱ ሄዝቦላህ የጦር መሳሪያ ለማስተላለፍ የሚደረጉ ጥረቶችንም በአውሮፕላኖቿ ማምከኗን ደጋግማ ገልፃለች።
ሶሪያ ግን በአየር መቃወሚያ ስርአቷ ላይ እስራኤል መጨነ ሰፊ ጥቃት ማድረሷን ነው የምትገልፀው።
እስራኤል በሶሪያ ምድር እንዳሻት የአየር ጥቃት እንድትፈፅም ከሩስያ ጋር የነበራት ግንኙነት ረድቷታል።
ከበሽር አል አሳድ ጎን የተሰለፈችው ሞስኮ የደማስቆን የአየር ክልል በስፋት ተቆጣጥራለች፤ ቴል አቪቭ የሶሪያን የአየር ክልል እያለፈች ጥቃት እንድትፈፅምም ፈቅዳለች።
አሁን ላይ ግን የእስራኤልና ሩስያ ግንኙነት እየሻከረ በመምጣቱ የአየር ድብደባው ጋብ ብሏል።
በዩክሬኑ ጦርነት ከኬቭ ጎን የተሰለፈችው እስራኤል የሶሪያ ሰማይ ላይ የቀደመውን ነፃነቷን እያገኘች አይደለም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የአየር ድብደባው ዜና መሰማት ጀምሯል። እስራኤል በ1967ቱ የስድስት ቀኑ ጦርነት የጎላን ኮረብቶችን ከሶሪያ ከወሰደች በኋላ ሀገራቱ ሰላም ርቋቸዋል።