የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ኢራንን በመረጃ ምንተፋ ከሰሰ
ቴህራን ሚስጢራዊ መረጃዎችን በመስረቅ አሰራጭታለች በሚል የከሰሰው ቡድኑ ቀጥተኛ ማስረጃ ግን አላቀረበም
ማይክሮሶፍት የውጭ ሃይሎች የ2024ቱን የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለማወክ ሙከራ እያደረጉ ነው ብሏል
የዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ኢራንን በመረጃ ምንተፋ ከሰሰ።
የሪፐብሊካን ፓርቲ የቅስቀሳ ቡድኑ የኢራን መንግስት ሚስጢራዊ መረጃዎችን ሰርቆ አሰራጭቷል የሚል መግለጫን ቢያወጣም ቀጥተኛ ማስረጃን ግን አላቀረበም።
ቴህራንን የሚከሰው መግለጫ የወጣው ፖለቲኮ በሀምሌ ወር ከማይታወቁ ምንጮች በትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ዙሪያ ታማኝ ሰነዶች ደርሶኛል የሚል ዘገባን ባወጣ ማግስት ነው።
ትራምፕ ምክትላቸው ሆነው እንዲወዳደሩ በመረጧቸው ጄዲ ቫንስ ዙሪያም የተለያዩ መልዕክቶች እንደደረሱት ፖለቲኮ ዘግቦ ነበር።
የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን “እነዚህ ሰነዶች ለአሜሪካ አፍራሽ አመለካከት ካላቸው የውጭ ሀይሎች በህገወጥ መንገድ ነው የተገኙት፤ በ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ በመግባት የዴሞክራሲያዊ ሂደቱን ለማወክ ያለሙ ናቸው” ብሏል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በራሳቸው የማህበራዊ ትስስር ትሩዝ ሶሻል ባወጡት መግለጫም የምርጫ ቅስቀሳ ቡድናቸው ድረገጽ በኢራን የመረጃ ዘራፊዎች መጠቃቱን ገልጸዋል።
የተሰረቁት ሰነዶች ማንኛውም ሰው ሊያገኛቸው የሚችሉ ናቸው ያሉት ትራምፕ፥ የመረጃ ስርቆቱ እንዴትና በየትኛው የመረጃ መንታፊ ቡድን እንደተከናወነ ግን በዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል።
የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ማይክሮሶፍት ባለፈው አርብ ያወጣውን መረጃም አጣቅሶ አቅርቧል።
የማይክሮሶፍት ተመራማሪዎች ከኢራን ጋር ግንኙነት ያለው የመረጃ መንታፊ ቡድን በሰኔ ወር ከህዳሩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጋር ግንኙነት ያላቸው የከፍተኛ ባለስልጣናት አካውንቶችን ሰብሮ ለመግባት መሞከሩን መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
የማይክሮሶፍት መረጃ የትኞቹ የአሜሪካ ባለስልጣናት በመረጃ መንታፊ ቡድኑ ኢላማ እንደተደረጉ ግን አልጠቀሰም ይላል የሬውተርስ ዘገባ።
በመንግስታቱ ድርጅት የኢራን ቋሚ መልዕክተኛ ግን “የኢራን መንግስት በቀጣዩ የአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ የመግባትም ሆነ መረጃዎችን የመመንተፍ ፍላጎት የለውም” የሚል መግለጫ አውጥቷል።
ቴህራን ለሚቃጡ ጥቃቶች ምላሽ የመስጠትና የመከላከል የሳይበር አቅም ማዳበሯን በመጥቀስም በሌሎች ሀገራት ላይ ግን የሳይበር ጥቃት መፈጸም እንደማትፈልግ አብራርቷል።
በስልጣን ዘመናቸው ከኢራን ጋር ግንኙነታቸውን ያሻከሩት ትራምፕ በሀምሌ ወር የተፈጸመባቸው የግድያ ሙከራ ከቴህራን ጋር ግንኙነት እንዳለው ሲኤንኤን ባለፈው ወር ባወጣው ዘገባ ማመላከቱ የሚታወስ ነው።
ቴህራን ግን በትራምፕ የግድያ ሙከራ ሴራ እጇ አለበት በሚል የቀረበባትን ክስ ማጣጣሏ አይዘነጋም።