ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ ጥቃት ካደረሰ መሪዎቹ የናስራላህ እጣ ይጠብቃቸዋል - እስራኤል ካትዝ
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ሄዝቦላህ ከሰሞኑ ወደ እስራኤል ድሮኖችን መላኩን ተናግረዋል
ካትዝ በሊባኖስ የሚገኘውን የእስራኤል ጦር ማዘዣ በዛሬው እለት ጎብኝተዋል
እስራኤል ከሊባኖሱ ሄዝቦላህ ጋር ዳግም ጦርነት ልትጀምር እንደምትችል አስጠነቀቀች።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ዛሬ በሊባኖስ የሚገኘውን የእስራኤል ጦር ማዘዣ የጎበኙ ሲሆን ከከፍተኛ አዛዦችም ጋር መክረዋል።
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ሄዝቦላህ ከሰሞኑ ከሊባኖስ ወደ እስራኤል ድሮኖችን ለመላክ መሞከሩን መግለጻቸውን ታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘግቧል።
"ለሄዝቦላህ እና የሊባኖስ መንግስት ግልጽ መልዕክት ማድረስ እፈልጋለሁ፤ እስራኤል ከሊባኖስ የድሮን ጥቃት ሙከራ እንዲደረግ አትፈቅድም፤ ወደ ጥቅምት 7ቱ (2023) እውነታ መመለስ አንፈልግም" ብለዋል።
ሄዝቦላህ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሶ ወደ ቀደመው ጥቃቱ ከተመለሰ የወቅቱ የቡድኑ መሪዎች የሀሰን ናስራላህ እጣ ይጠብቃቸዋል ሲሉም አስጠንቀዋል።
እስራኤል እና የሊባኖሱ ሄዝቦላህ በአሜሪካ አደራዳሪነት በህዳር ወር 2024 የ60 ቀናት ተኩስ አቁም ስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።
የእስራኤል ጦር በሊባኖስ የሚፈጽመውን የአየር ጥቃት እና የድንበር ላይ የተኩስ ልውውጡን ያስቆመው ስምምነት ባለፈው ሳምንት ተጠናቆ እስከ የካቲት 18 2025 ድረስ ተራዝሟል።
ለተኩስ አቁም ስምምነቱ በሚገባ አለመፈጸምና መጣስ ሁለቱም ወገኖች እርስ በርስ ሲካሰሱ ቆይተዋል።
በህዳር ወር በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት የእስራኤል እና የሄዝቦላህ ሃይሎች ከደቡባዊ ሊባኖስ እስከ ፈረንጆቹ ጥር 26 እንዲወጡና አካባቢውንም የሊባኖስ ብሔራዊ ጦር እና የተመድ የሰላም አስከባሪ ሀይሎች እንዲቆጣጠሩት መስማማታቸውን ሬውተርስ አስታውሷል፡፡
እስራኤል የሊባኖስ መንግስት ስምምነቱን በሚገባ አላስፈጸመም በሚል ወታደሮቿን በተቀመጠው ጊዜ እንደማታስወጣ ገልጻለች፤ በተራዘመው ስምምነትም ጦሯን ከሊባኖስ ታስወጣለች ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው።
ሄዝቦላህ በበኩሉ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተፈጻሚ የሚሆነው በደቡባዊ ሊባኖስ ብቻ መሆኑን በመጥቀስ እስራኤል ወታደሮቿን የማስወጣት ፍላጎት የላትም ሲል ይወቅሳል።
የሊባኖሱ ቡድን ከሰሞኑ ወደ እስራኤል ድሮኖችን ልኳል በሚል በእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር በኩል ለቀረበበት ወቀሳ ምላሽ አልሰጠም።