እስራኤል ከሄዝቦላህ ጋር በደረሰችው የተኩስ አቁም ስምምነት ቀን ማብቂያ ከሊባኖስ እንደማትወጣ አስታወቀች
በአሜሪካ አደራዳሪነት የተፈረመው ስምምነት እስራኤል በሁለት ወራት ውስጥ ከደቡባዊ ሊባኖስ ጦሯን ሙሉ ለሙሉ እንድታስወጣ ያዛል
ሄዝቦላህ እና እስራኤል የተፈራረሙት የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት በነገው ዕለት ይጠናቀቀቃል
የእስራኤል መንግስት ከሄዝቦላህ ጋር ለወራት የገባበትን ግጭት ያስቆመውን የተኩስ አቁም ስምምነት በመጣስ ወታደሮቹ በእሁዱ ቀነ ገደብ ከሊባኖስ እንደማይወጡ ገልጿል።
እስራኤል በስምምነቱ መሰረት ሙሉ ጦሯን በነገው እለት ከደቡባዊ ሊባኖስ ታስወጣለች ተብሎ ቢጠበቅም የእስራኤል መንግስት የተወሰኑ ሀይሎች በደቡባዊ ሊባኖስ እንደሚቆዩ በመግለጽ ሊባኖስን ስምምነቱ ማስፈጸም ባለመቻሏ ጥፋተኛ አድርጓል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ የሊባኖስ መንግስት ስምምነቱን ተግባራዊ ባለማድረጉ የእስራኤል ጦር ሙሉ ለሙሉ እንደማይወጣ እና ጦሩን የማስወጣት ሂደት ቀስ በቀስ እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡
የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ብሪያን ሂዩዝ አሜሪካ ከአጋሮች ጋር በመሆን አጭር እና ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ማራዘሚያ ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራች ነው ብለዋል።
ቃል አቀባዩ “ሄዝቦላህ የሊባኖስን ህዝብ ወይም ለጎረቤቶቹ ደህንነት ስጋት የመፍጠር አቅም እንደሌለው ማረጋገጥ የሁሉም ወገኖች ግብ" መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም “የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ከማዕከላዊ የሀገሪቱ ክፍሎች መውጣት መጀመሩ የሚበረታታ ነው፤ ጦሩ ሙሉ ለሙሉ እንዲወጣ የተኩስ አቁም ማራዘሚያን ገቢራዊ እናደርጋለን” ነው ያሉት፡፡
የሊባኖስ የጸጥታ ቢሮ ምንጭ ለሲኤንኤን እንደገለጹት እስራኤል በሊባኖስ ከ60 ቀናት በላይ ጦሯን ለማቆየት ማሰቧን ይፋዊ ማሳሰቢያ ለሀገሪቱ አልሰጠችም፡፡
በህዳር ወር በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት የእስራኤል እና የሂዝቦላህ ሃይሎች ከደቡብ ሊባኖስ በፈረንጆቹ ጥር 26 ለማስወጣት አካባቢውንም የሊባኖስ ብሔራዊ ጦር እና የተመድ የሰላም አስከባሪ ሀይሎች እንዲቆጣጠሩት ተስማምተዋል፡፡
ሄዝቦላህ ባሳለፍነው ሀሙስ ባወጣው መግለጫ የእስራኤል ጦር ስምምነቱ ከሚጠናቀቅበት እሁድ አሳልፎ በሊባኖስ የሚቆይ ከሆነ ተኩስ አቁሙን በይፋ እንደጣስ ይቆጠራል ሲል አስጠንቅቋል።
በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ትላንት ምሽት የተሰበሰበው የእስራኤል የደህንነት ካቢኔ የእስራኤል መንግስት ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የእስራኤል ወታደሮች ቢያንስ ለተጨማሪ 30 ቀናት በሊባኖስ እንዲቆዩ እንደሚፈልግ ማሳወቁን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡