ሃማስ በጋዛ በምድር ውስጥ የገነባው ረጅምና ውስብስብ ዋሻ ለእስራኤል እግረኛ ጦር ፈታኝ እንደሚሆን ይገመታል
እስራኤል በጋዛ ድንበር “የሃማስን ግዙፍ ዋሻ” ማግኘቷን አስታወቀች።
ኢሬዝ በተሰኘው የእስራኤልና ጋዛ መተላለፊያ መግቢያው የተገኘው ዋሻ ሃማስ ጥቅምት 7 2023 በእስራኤል ላይ ጥቃት ሲከፍት ተጠቅሞበት ነበር ተብሏል።
ቴል አቪቭ ወደ ጋዛ ስትገባም የሃማስ ታጣቂዎች መደበቂያ ቦታዎችን ማውደም አንዱ አላማዋ እንደነበር ይታወሳል።
መውጫው ከእስራኤልና ጋዛ ድንበር በመቶ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል የተባለው የሃማስ ዋሻ እስከ 4 ኪሎሜትር ድረስ ርዝመት እንዳለው ነው የእስራኤል ጦር ያስታወቀው።
መግቢያው 50 ሜትር ጥልቀት ያለውና እየሰፋ የሚሄደው ዋሻ በኮንክሪት እና በብረት የተገነባ መሆኑንም የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳኔል ሃጋሪ ገልጸዋል።
የዋሻው ውስጣዊ ክፍል ስፋትና ርዝመቱ 3 ሜትር በመሆኑም ተሽከርካሪዎች ጭምር መንዳት ያስችላል ነው ያሉት።
ቃል አቀባዩ የሃማስ መሪው ያህያ ሲንዋር ወንድም ሞሀመድ ሲንዋር በዚሁ ዋሻ ተሽከርካሪ ውስጥ ሆነው ሲጓዙ ያሳያል ያሉትን ምስል ለጋዜጠኞች አሳይተዋል።
ረጅሙ ዋሻ ከእስራኤል ድንበር እስከ ሰሜናዊ ጋዛ ድረስ ከእይታ ተሰውሮ መጓዝ የሚያስችል እንደነበርም በመግለጫቸው አብራርተዋል።
“ይህ ዋሻ (በኢሪዝ የሚገኘው) በጋዛ ካገኘናቸው ዋሻዎች ሁሉ ትልቁ ነው” ያሉት ዳኔል ሃጋሪ፥ ዋሻውን በቁጥጥር ስር ለማዋል ውጊያ ስለመደረጉ አላብራሩም።
ሃማስ ግን በእስራኤል ጦር ተይዟል ስለተባለው ረጅም ዋሻ የሰጠው ምላሽ የለም።
ቡድኑ በጋዛ ምድር ውስጥ ለአመታት የገነባው ረጅምና ውስብስብ ዋሻ የእስራኤል ጦርን ዘመቻ እንደሚፈትነው ይጠበቃል።
የታገቱ ሰዎችም በእነዚህ ዋሻዎች ውስጥ እንደሚኖሩ የሚታመን ሲሆን፥ የጦርነቱ እየተባባሰ መሄድ እስራኤላውያን የታጋቾች ቤተሰቦችን ስጋት ላይ ጥሏል።