አሜሪካ ለምን የፕሬዝዳንቷን ጉብኝት እንዳራዘመች እስካሁን ይፋ አላደረገችም
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሳውዲ እና እስራኤል ጉብኝታቸውን አራዘሙ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በያዝነው ሰኔ ወር ላይ ሳውዲ አረቢያን እና እስራኤልን እንደሚጎበኙ ከዚህ በፊት ይፋ አድርጋ ነበር።
ይሁንና የፕሬዝዳንቱ ወደ ሪያድ እና ቴልአቪቭ ሊያደርጉት ያቀዱትን ጉብኝት ለአንድ ወር ያራዘሙ ሲሆን ለጉብኝቱ መራዘም ምክንያት እንዳልተጠቀሰ ሮይተርስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በዚሁ በተያዘው ሰኔ ወር ላይ ጀርመንን እና ስፔንን እንደሚጎበኙ ከዚህ በፊት ይፋ የጠደረገ ቢሆንም ባልታወቀ ምክንያት ጉብኝቱ ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ዘገባው አክሏል።
የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ፕሮግራም ቀኑ አለመታወቁን ተከትሎ ለሶስተኛ ጊዜ ሊራዘም እንደሚችል ሮይተርስ ዲፕሎማቲክ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
የአሜሪካው የመረጃ ስለላ ተቋም ሲአይኤ በፈረንጆቹ 2018 ላይ የሳውዲ አልጋ ወራሽ መሀመድ ሰልማን ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ እንዲገደሉ ቀጥተኛ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል ማለቱ ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በጋዜጠኛ ካሾጊ ግድያ ዙሪያ አልጋ ወራሽ መሀመድ ሰልማንን በንግግር መወረፋቸውን ተከትሎ የሳውዲ እና ዋሸንግተረን ግንኙነት እንደከዚህ በፊቱ እንዳልሆነ ይጠቀሳል።
በሚቀጥለው ወር ይካሄዳል የጠባለው የፕሬዝዳንት ባይደን ጉብኝት ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻሻል አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ተስፋ ተጥሎበታል ተብሏል።
ይህ በዚህ እንዳለ በመስከረም 11ዱ የአልቃይዳ የሽብር ጥቃት ሰላባ የሖኑ አሜሪካዊያን ቤተሰቦች ለፕሬዝዳንት ባይደን በጻፉት ደብዳቤ በሪያድ ቆይታቸው ከሳውዲ መንግስት ጋር በድርጊቱ በተሳተፉ አካላት ላይ ተጠያቂነት በሚሰፍንበት ሁኔታ እንዲወያዩ ጠይቀዋል።