የእስራኤል የጦር ካቢኔ ሚኒስትር ቤኒ ጋንዝ ስልጣን ሊለቁ እንደሚችሉ ተናገሩ
ሚኒስትሩ ኔታንያሁ የድህረ ጋዛ ጦርነትን በተመለከተ ግልፅ እቅድ እንዲያቀርቡ አሳስበዋል
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትርም ኔታንያሁ እስራኤል የሲቪል አስተዳደር የመቆጣጠር ፍላጎት እንደሌላት ግልጽ ማድረግ አለባቸው ብለዋል
የእስራኤል የጦር ካቢኔ ሚኒስትር ቤኒ ጋንዝ ስልጣን ሊለቁ እንደሚችሉ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ካበቃ በኋላ እስራኤል የሚኖራትን ድርሻ በተመለከተ ግልጽ እቅድ ካላቀረቡ ነው ጋንዝ ስልጣኔን እለቃለሁ ያሉት።
የጦር ካቢኔ ሚኒስትሩ እቅዱ ስድስት “ስትራቴጂካዊ ግቦችን” ማሳካት እንዳለበትም አሳስበዋል።
በጋዛ የሃማስ መሪነት ማክተም፣ የታጋቾች መለቀቅ እና በጋዛ የሲቪል አስተዳደር የሚቋቋምበትን ሁኔታ ማመቻቸት ቤኒ ጋንዝ ካስቀመጧቸው አንኳር ነጥቦች መካከል ይጠቀሳሉ።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንትም ከቀናት በፊት ኔታንያሁ እስራኤል በጋዛ የሲቪል አስተዳደሩን የመቆጣጠር ፍላጎት እንደሌላት ለአለም ግልጽ ማድረግ አለባቸው ማለታቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
ጋላንት እና ጋንዝ እስራኤል በጋዛ ወታደራዊ እንቅስቃሴውን የሚቀጥል ከሆነ ለሀገሪቱ አደጋ ነው ብለው እንደሚያምኑ ሲናገሩ ተደምጧል።
ኔታንያሁ እና ቀኝ ዘመም አጣማሪ ፓርቲዎቻቸው አመራሮች ግን ሃማስን ለመደምሰስ እርምጃው መቀጠሉ ተገቢ ነው ይላሉ።
ለኔታንያሁ “የእስራኤል ህዝብ በአይነ ቁራኛ እየተመለከተዎት ነው” የሚል መልዕክታቸውን በቴሌቪዥን ያስተላለፉት የጦር ካቢኔ ሚኒስትሩ ቤኒ ጋንዝ፥ “ከሀገር ይልቅ የግል ጉዳይ ካስቀደሙ ተባብረን እንታገልዎታለን” ማለታቸውም ተዘግቧል።
ሚኒስትሩ በጋዛ የሚገኙ ታጋቾች እና የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያንን ወደ ሰሜናዊ ጋዛ የሚመለሱበትን ቀነ ገደብም አስቀምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በሰጡት ምላሽ፥ የቤኒ ጋንዝ ፍላጎት እስራኤልን ለሽንፈት የሚዳርግ፣ ታጋቾችን አደጋ ላይ የሚጥልና ሃማስን በሽብር ተግባሩ እንዲገፋበት የሚፈቅድ ነው በሚል ተቃውመውታል።
ሃማስ በጥቅምት 7 በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ባደረሰ ማግስት የተቋቋመው የእስራኤል የጦር ካቢኔ በኔታንያሁ ላይ ጫናው በርትቷል።
የእስራኤል የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሄርዚ ሃሌቪም ኔታንያሁ ድህረ የጋዛ ጦርነት እቅድን ይፋ እኝዲያደርጉ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የእስራኤል ወታደሮች ሃማስ ሙሉ በሙሉ ተደምስሶባታል ወደተባለችው ሰሜናዊ ጋዛ ጃባሊያ መመለሳቸው የእስራኤል ጦር ከጋዛ የመውጣት የቅርብ ጊዜ እቅድ እንደሌለው ማሳያ ነው ተብሏል።
ኔታንያሁ ከውስጥም ከውጭም ጫናው ቢበዛባቸውም የራፋህ ዘመቻውን ለመጀመር ቅድመ ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ ነው።
ከደቡባዊ ጋዛ ከተማዋ ከ800 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን እንዲወጡ መደረጉን የጠቀሰው የተመድ የፍልስጤማውያን የእርዳታ ድርጅት፥ ለዳግም መፈናቀል ሲዳረጉም ሞትና እንግልቱ ቀጥሏል ብሏል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫኒ ዛሬ ቴል አቪቭ ሲገቡም ኔታንያሁ በራፋህ የሚጀምሩት ጦርነት አሳሳቢነትን ያነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።