2 ሚሊየን ፍልስጤማውያን ጦርነትን ሽሽት ከቀያቸው ቢፈናቀሉም ሞትና ረሃቡ ባሉበት እየተከተላቸው ነው
የፍልስጤሙ ሃማስ ወደ እስራኤል በመዝለቅ ያልተጠበቀ ጥቃት ካደረሰ ዛሬ ስድስት ወር ሆኖታል።
ከ1 ሺህ 100 በላይ ዜጎቿ የተገደሉባት እስራኤል ከሃማስ ጥቃት በኋላ በጋዛ እየወሰደችው ያለው ድብደባም አልቆመም።
በጦርነቱ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ፍልስጤማውያን የሚኖሩበት ጋዛ ሰርጥ የአለማችን ከባድ ስብአዊ ቀውስ የተከሰተበት ስፍራ ወደመሆን ተቀይሯል።
እስራኤል በየቀኑ በምትፈጽማቸው የአየር ድብደባዎች ከ33 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ህይወት ተቀጥፎ ከ75 ሺህ በላይ ሰዎች ቆስለዋል።
ህይወታቸው ካለፈ ፍልስጤማውያን መካከል ከ73 በመቶ በላዩ ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውንም የጋዛ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
ከ2 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያንን ጦርነቱን ሽሽት ከቀያቸው ቢፈናቀሉም ሞትና ረሃቡ ባሉበት እየተከተላቸው ነው።
እስራኤል በአየር ድብደባ እና በእግረኛ ጦሯ የተቀናጀ እርምጃ ከ13 ሺህ በላይ "ሽብርተኞች"ን መግደሏን ያስታወቀች ሲሆን፥ የጋዛ ባለስልጣናት እና አለማቀፍ ተቋማት ግን አብዛኞቹ የተገደሉት ሰዎች ንጹሃን መሆናቸውን በመጥቀስ ተቃውሟቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
ዛሬ ስድስተኛ ወሩን በያዘው ጦርነት የደረሰውን ሰብአዊ ጉዳት በቀጣዩ ምስል በዝርዝር ይመልከቱ፦