እስራኤል በሶሪያ ከኢራን ጋር ግንኙነት አላቸው ባለቻቸው ሃይሎች ላይ ጥቃት ፈጸመች
ባኒያስ በተባለችው የወደብ ከተማ በተፈጸመው የሚሳኤል ጥቃት የንብረት ውድመት ደርሷል ተብሏል
እስራኤል ከ2012 ጀምሮ የኢራንን በሶሪያ መስፋፋት ይገታሉ ያለቻቸውን የአየር ጥቃቶች ስትፈጽም ቆይታለች
እስራኤል በሶሪያ የአየር ጥቃት መፈጸሟ ተነገረ።
በሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ በምትገኘው ባኒያስ የተሰኘች ከተማ የተፈጸመው ጥቃት መጠነኛ የንብረት ውድመት ማስከተሉን የሶሪያ ብሄራዊ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የሶሪያ አየር ሃይል መጠናቸውን ያልጠቀሳቸውን ሚሳኤሎች መትቶ መጣሉን አስታውቋል።
ጥቃቱ ከኢራን ጋር ግንኙነት ያላቸው ሃይሎች ላይ ያነጣጠረ እንደሚሆን ተገምቷል።
የሶሪያ ዋነኛው የነዳጅ ማጣሪያ የሚገኝባት የባኒያስ ከተማ አብዛኛውን የሀገሪቱን የነዳጅ ፍላጎት ታሟላለች።
የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከቦችም በወደብ ከተማዋ በተደጋጋሚ የሚታዩ ሲሆን እስራኤል እነዚህ መርከቦች ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን በቅርብ አመታት ውስጥ ፈጽማለች።
ተንታኞች የባኒያስ ወደብ ቴህራን ወደ ደማስቆ የጦር መሳሪያ የምታስገባበት መሆኑን ይገልጻሉ።
እስራኤሉ የደህንነት ተቋም ኢሜጅሳት ኢንተርናሽናል በ2017 የለቀቀው የሳተላይት ምስል በወደቧ አቅራቢያ የባለስቲክ ሚሳኤል ማምረቻ እንዳለና ይህም በኢራን ከሚገኙ የሚሳኤል ማምረቻዎች ጋር እንደሚመሳሰል ማስታወቁ ይታወሳል።
በሶሪያ የኢራንን መስፋፋት አልፈቅድም የምትለው እስራኤል እንደወትሮው ለዛሬው ጥቃትም ሃላፊነቱን እንደምትወስድ ከመናገር ተቆጥባለች።
ቴል አቪቭ ከፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ በሶሪያ እና ኢራቅ የሚገኙና ኢራን ታስታጥቃቸዋለች ብላ የምታምንባቸው ታጣቂዎች ላይ የአየር ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለፍልስጤሙ ቡድን አጋርነታቸውን ባሳዩ የሊባኖሱ ሄዝቦላህ እና በኢራቅ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ላይም ጥቃቷ አላባራም።
የሶሪያውን ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ የምትደግፈው ቴህራን የደማስቆን ወታደራዊ አቅም ለማጎልበት ወታደሮቿን ልካለች።
ኢራን በሶሪያ መንግስት ጥያቄ የላኳቸው ወታደሮች የማማከር ሚና ብቻ ነው ያላቸው ብትልም እስራኤል ግን የቴህራን ወደ ደማስቆ መዝለቅን በስጋት በመመልከት ጥቃቷን ቀጥላለች።