የቱርክ እና ጆርዳን ፕሬዝዳንቶች ከሰሞኑ በእስራኤል ላይ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በይፋ ጠይቀዋል
የእስራኤል ጥቃት ካልቆመ የአረብ ሀገራት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
ከ11 ወራት በፊት የፍልስጤሙ ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ ነበር በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት የተቀሰቀሰው፡፡
እስራኤል ሐማስ በሚንቀሳቀስበት ጋዛ ውስጥ ባደረሰችው ጥቃት ከ41 ሺህ በላይ ንጹሃን የተገደሉ ሲሆን አሁን ደግሞ ይህ ጦርነት ወደ ሊባኖስ ዞሯል፡፡
ይህን ተከትሎም እስራኤል በጋዛ በምትሰነዝረው ጥቃት ምክንያት በሚደርሱ ውድመቶች ንዴታቸውን ሲገልጹ የቆዩት የአረብ ሀገራት መሪዎች በሊባኖስ የተጀመረው ጦርነት እንዲቆም እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡
የእስራኤል ዋነኛ አጋር የምትባለው አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት በሂዝቦላህ እና እስራኤል መካከል የተጀመረው ጦርነት እንዲቆም የሶት ሳምንታት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡
የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተኩስ አቁም ስምምነት እቅዱን ውድቅ ያደረጉ ሲሆን ሂዝቦላህ እስከሚሸነፍ ድረስ እንደሚዋጉም ተናግረዋል፡፡
ይህን ተከትሎም የአረብ ሀገራት ቁጣ የጨመረ ሲሆን በኒዮርክ እየተካሄደ ባለው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በሚያደርጓቸው ንግግሮች ላይ እያንጸባረቁ ናቸው፡፡
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን፣ የጆርዳኑ ፕሬዝዳንት ንጉስ አብደላህ ሁለተኛ እና ሌሎችም እስራኤል በሊባኖስ የጀመረችው ጥቃት እንዲቆም አስጠንቅቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን እንዳሉት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እንደ አዶልፍ ሂትለር ዓለም ተረባርቦ ሊያስቆመው ይገባል ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ግብጽ፣ ኳታር፣ ኢራቅ እና ሌሎችም ሀገራት የእስራኤል ድርጊት መካከለኛው ምስራቅን ወደ ሙሉ ጦርነት ሊያስገባው የሚችል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የጀርመኑ ዶቸቪሌ እንግሊዘኛ ክፍል በእስራኤል ጥቃት የተበሳጩት የአረብ ሀገራት ከብስጭት ቃላት ያለፈ እርምጃ ይወስዱ ይሆን? ሲል የመካከለኛው ምስራቅ ተንታኞችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
እንደ ተንታኞቹ አስተያየት ከሆነ የአረብ ሀገራት በ197ዎቹ የነበረው የእስራኤል-አረብ ጦርነት አይነት ህብረት አሁን ላይ የመፈጠር እድሉ እጅግ የጠበበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዋና መቀመጫውን ኳታር ባደረገው የመካከለኛው ምስራቅ ምክር ቤት ዓለም አቀፍ ጥናት ዳይሬክተር የሆነው አደል አብደል ጋፋር እንዳሉት "የአረብ ሀገራት ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፣ ተመድን ጨምሮ በአረብ ሊግ እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል እስራኤልን ለመነጠል ብዙ ሞክረዋል፣ የንዴት ቃል ከመናገር የዘለለለ ነገር ያደርጋሉ ብዬ አልጠብቅም፣ ይህ ደግሞ እስራኤልን የምትፈልገውን ከማድረግ የሚያግዳት አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ግብጽ እና ኳታር እስራኤል እና ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ብዙ የጣሩ ሀገራት ቢሆኑም ጦርነቱ አንድ ዓመት ሊሆነው አንድ ሳምንት ብቻ ቀርቶታል፡፡
ከእስራኤል ጋር አዲስ የጦርነት ግምባር የፈጠረው ሂዝቦላህ የተኩስ አቁም ለማድረግ እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን ጦርነት እንድታቆም በቅድመ ሁኔታነት አስቀምጧል፡፡
መሰረቱን ዋሸንግተን ያደረገው የመካከለኛው ምስራቅ አጥኚ የሆነው ካሊድ ኤልጊንዲ በበኩሉ በእስራኤል-ሐማስ ጦርነት የተጎዱት ግብጽ እና ጆርዳን እስራኤል ጦርነቱን እንድታቆም በአሜሪካ በኩል ጨና ለመፍጠር እየሞከሩ ናቸው ብሏል፡፡
"የአረብ ሀገራት በጋዛ የነበረው አይነት ተመሳሳይ ነገር በሊባኖስም ይደግሙታል፣ ምክንያቱም አብዛኞቹ የአረብ ሀገራት ከአሜሪካ ጋር መልካም ግንኙነት አላቸው" ያሉት ተንታኙ ሀገራቱ በቀጥታ እስራኤል ጦርነቱን እንድታቆም ጥረት እንደማያደርጉም ተናግረዋል፡፡
"ምን አልባት የአረብ ሀገራት ጫና ለማድረግ ከተስማሙ ሊያደርጉ የሚችሉት በደቡብ አፍሪካ አነሳሽነት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በዓለም አቀፉ ጦር ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆኑ የተጀመረውን ጥረት ሊቀላቀሉ ይችሉ ይሆናል" ሲሉም ኤልጊንዲ ገልጸዋል፡፡
እስራኤል በጋዛ የዘር ማጥፋት ፈጽማለች በሚል በደቡብ አፍሪካ የቀረበውን ጥያቄ ከደገፉ የአረብ ሀገራት ውስጥ ሊቢያ፣ ቱርክ እና እራሷ ፍልስጤም ብቻ ናቸው፡፡
የተወሰኑ የአረብ ሀገራት ደግሞ ከዚህ በፊት ከእስራኤል ጋር የተደረጉ የተለያዩ ስምምነቶችን ሊሰርዙ እንደሚችሉ ቢያስጠነቅቁም ከአሜሪካ ሊመጣ የሚችል ጨናን በመፍራት እስካሁን ገፍተውበት አልሄዱም ተብሏል፡፡
በርካታ የአረብ ሀገራት ከእስራኤል ይልቅ ኢራንን የበለጠ እንደሚጠሉም ይህ ተንታኝ የተናገሩ ሲሆን የአረብ ሀገራት በጋራ በእስራኤል ላይ ጫና የመፍጠር አቅማቸው አነስተኛ መሆኑም ተንታኙ ተናግረዋል፡፡
የአረብ ሀገራት በእስራኤል ላይ ጫና ከመፍጠር ይልቅ እያወሩ ያሉት ለተፈናቃዮች የሰብዓዊ እርዳታዎች እንዲቀርቡ፣ የተዘጉ ድንበሮች እንዲከፈቱ እና ሌሎች ድጋፎች እንዲደረግ እየጠየቁ ናቸውም ተብሏል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ የተፈጠረው ቀውስ የሚቆመው በዋናነት በአረብ ሀገራት የህብረት ጫና ሳይሆን እንደ አሜሪካ እና ሌሎች ለእስራኤል የጦር መሳሪያ ድጋፍ የሚያደርጉ ሀገራት ጫና ካደረጉ ብቻ ሊሆን እንደሚልም ተንታኞቹ ተናግረዋል፡፡