የእስራኤል ጦር ኢታማዦር ሹም ሀለቪ ከጥቅምቱ 7ቱ የጸጥታ ክፍተት ጋር በተያያዘ ከኃላፊነት እንደሚለቁ አስታወቁ
"ጥቅምት 7 በእኔ እዝ ስር የነበረው የእስራኤል ጦር የእስራኤል ዜጎችን ከጥቃት ማዳን ሳይችል ቀርቷል" ሲሉ ሀለቪ ለመከላከያ ሚኒስቴር ባቀረቡት የመልቀቂያ ደብዳቤ ላይ ጽፈዋል
ሀሊቪ ስልጣን እንደሚለቁ ይፋ ያደረጉት እስራኤልና ሀማስ ለ15 ወራት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም የሚያስችል ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ነው
የእስራኤል ጦር ኢታማዦር ሹም ሀለቪ ከጥቅምቱ 7ቱ የጸጥታ ክፍተት ጋር በተያያዘ ከኃላፊነት እንደሚለቁ አስታወቁ።
የእስራኤል ጦር ኢታማዦር ሹም ኸርዚ ሀለቪ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ጥቅምት 7፣2023 ድንበር ጥሶ በእስራኤል ላይ ጥቃት በፈጸመቀት ወቅት ለነበረው የጸጥታ ክፍተት ኃላፊነት በመውሰድ የካቲት መጨረሻ ከኃላፊነት እንደሚነሱ በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
ሀማስ በአንድ ቀን ውስጥ በታሪክ ከባድ የተባለ ጥቃት በእስራኤል ላይ ካደረሰ በኋላ ስልጣን ይለቃሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት ሀለቪ ከጥቅምት ሰባቱ ጥቃት ጋር በተያያዘ በጦሩ ላይ የቀረበውን ምርመራ ለማጠናቀቅ እና ጦሩ ለጸጥታ ስጋቶች ያለውን ዝግጁነት ለማጠናከር ሲሉ ጊዜ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
የጦሩን እዝ ለተኪያቸው እንደሚያስረክቡ የገለጹትን ሀለቪን ማን እንደሚተካቸው አልታወቀም።
በጥቃቱ ከፍተኛ የህዝብ ቁጣ ቢቀሰቀስም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መንግስት 1200 ሰዎች እንዲገደሉና 250 ታግተው እንዲወሰዱ ምክንያት ለሆነው የጸጥታ ክፍተት ምርመራ እንዳደረግ የቀረበውን ጥሪ አልተቀበሉትም።
"ጥቅምት 7 በእኔ እዝ ስር የነበረው የእስራኤል ጦር የእስራኤል ዜጎችን ከጥቃት ማዳን ሳይችል ቀርቷል" ሲሉ ሀለቪ ለመከላከያ ሚኒስቴር ባቀረቡት የመልቀቂያ ደብዳቤ ላይ ጽፈዋል።
ሀሊቪ አክለውም እስራኤል የብዙ ሰዎች ህይወት ገብራለች፣ የታገቱተም ቢሆኑ "በስጋና በነፍስ" ቆስለዋል ብለዋል።
ለአራት አስርት አመታት ያገለገሉት ሀለቪ "ለአሳዛኙ ውድቀት ኃላፊነት መውሰዴ በየቀኑ ደቂቃ በደቂቃ፣ ሰአት በሰአት እና በቀሪው ህይወቴም ይከተለኛል"ብለዋል። ሀለቪ በቴሌቪዥን በተላለፈ መልእክት ጥቅል እና ግልጽ ምርመራ ተካሂዶ ውጤቱ ለመከላከያ ሚኒስቴርና እንደአስፈላጊነቱ ለህዝብ እንደሚቀርብ ቃል ገብተዋል።
ሮይተርስ መአሪቭ ዜናን ጠቅሶ እንደዘገበው የባህር ኃይል እና የአየር ኃይል ኃላፊዎችም የስልጣን መልቀቂያቸውን በቅርቡ ያስገባሉ ተብሏል።
ሀለቪ ባለፈው ህዳር ወር ከተባረሩት ከቀድሞው መከላከያ ሚኒስተር ዩአብ ጋላንት እና ከተወሰኑ ሚኒስትሮች ጋር ለኦሮቶክስ ተማሪዎች ከተሰጠው ለውትድርና ያለመመልመል መብት ጋር በተያያዘ አለመግባባት ውስጥ ገብተው ነበር።
በርካታ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ከጥቅምቱ ጥቃት ጋር በተያያዘ ኃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው የለቀቁ ሲሆን የጦሩ የደቡብ ዕዝ መሪ ሜጄር ጀነራል ዮራን ፍንቄልማንም እንደሚለቁ አሳውቀዋል።
ሀሊቪ ስልጣን እንደሚለቁ ይፋ ያደረጉት እስራኤልና ሀማስ ለ15 ወራት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም የሚያስችል ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ነው። የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊ በሆነት የመጀመሪያ ቀን ሶስት የእስራኤል ታጋቾች የተለቀቁ ሲሆን 90 ፍልስጤማውያን እስረኞች ተለቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የሀሊቪን መልቀቂያ ተቀብለውታል ተብሏል።