እስራኤል የተቋረጠውን የጋዛ ተኩስ አቁም ድርድር ዳግም ለማስጀመር ልኡኳን ወደ ዶሃ ልትልክ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሞሳድና ሌሎች የደህንነት ባለሙያዎችን ለመላክ ውሳኔ አሳልፈዋል
በሌላ በኩል እስራኤል በጋዛ በ24 ስአት ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ70 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል
እስራኤል በጋዛ ታግተው የሚገኙ ዜጎችን ለማስለቀቅና የተኩስ አቁም ድርድሩን ዳግም ለማስጀመር ልኡኳን ወደ ኳታር ልትልክ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ልኡካኑ የእስራኤል የደህንነት ኤጀንሲ (አይኤስኤ)፣ የእስራኤል ጦር እና የስለላ ተቋሙን ሞሳድ ባለሙያዎች ያካተተ ነው ብሏል።
እስራኤልና ሃማስ 16ኛ ወሩን የያዘውን የጋዛ ጦርነት ለማስቆም ሲያደርጉት የነበረውን ይፋዊ ድርድር ካቋረጡ ወራት ቢቆጠሩም ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር በማድረግ ላይ መሆናቸው ተገልጿል።
በኳታር በቅርቡ ዳግም ይጀምሩታል ተብሎ የሚጠበቀው ድርድር ተሰናባቹ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ካቀረቡት ምክረሃሳብ ጋር የተቀራረበ መሆኑን ሲኤንኤን ዲፕሎማቲክ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
ባይደን በግንቦት ወር ያቀረቡት የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ በሶስት ምዕራፎች የተከፋፈለ እንደነበር ይታወሳል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ለስድስት ሳምንታት የሚቆይ ሲሆን የእስራኤል ወታደሮች ህዝብ ከበዛባቸው የጋዛ አካባቢዎች እንዲወጡ የሚጠይቅ ነው። በጋዛ የሚገኙ ሴት እና አዛውንት ታጋቾች እንዲለቀቁና በምትኩም እስራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን እስረኞችን እንድትፈታ የሚያደርግ ነው።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ሲተገበር የእስራኤል ወታደሮች "ፊላደልፊያ ኮሪደር" በተሰኘው የጋዛ እና ግብጽ ድንበር በጊዜያዊነት ይቆያሉ የሚለው ሃሳብ በነሃሴ ወር ተጀምሮ የነበረውን ድርድር ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል። ሃማስ የእስራኤል ወታደሮች ሙሉ በሙሉ ከድንበር ይውጡ ማለቱ ይታወሳል።
ከዚህ የባይደን የባለሶስት ምዕራፍ የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ አለመሳካት ከወራት በኋላ ኳታር እስራኤልና ሃማስን የማደራደር ሚናዋን ማቋረጧን መግለጿ ይታወሳል።
ሁለቱም ተፋላሚ ሀይሎች ከ45 ሺህ 500 በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈውን ጦርነት ለማስቆም የሚደረጉ ንግግሮች ለመቋረጣቸው እርስ በርስ ይካሰሳሉ።
የእስራኤል ታጋቾች እና የጠፉ ሰዎች ቤተሰቦች የመሰረቱት ፎረም ኔታንያሁ ልኡካቸውን ወደ ዶሃ ለመላክ ውሳኔ ማሳለፋቸውን በማድነቅ "ይህን ጠባብ እድል አሁንም ልናባክነው አይገባም" የሚል መግለጫ አውጥቷል።
እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ያለው ጥቃት መጠናከር የታጋቾቹን በህይወት የመገኘት ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ እየከተተው ነው ያሉ የታጋቾቹ ቤተሰቦች ድምጻቸውን ማሰማታቸውን ቀጥለዋል።
በሌላ በኩል እስራኤል በትናንትናው እለት ብቻ በጋዛ በፈጸመችው 34 የአየር ጥቃት ከ70 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉን የጋዛ የመንግስት ሚዲያ ቢሮ አስታውቋል። ከሟቾቹ ውስጥም የጋዛ ፖሊስ አዛዥ ማህሙድ ሳላህ ይገኝበታል ተብሏል።
የእስራኤል ጦር ከካን ዩኒስ በስተምዕራብ በምትገኘው አል ማዋሲ የተፈጸመው የአየር ጥቃት የደህንነት መረጃዎች ላይ የተመረኮዘ መሆኑን በመጥቀስ የፖሊስ አዛዡን ጨምሮ ንጹሃን ስለመገደላቸው የቀረበበትን ወቀሳ አስተባብሏል።