ከእስራኤል እስር ቤቶች የሚወጡ ፍልስጤማውያን ከፍተኛ አዕምሯዊ እና አካላዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ተገለጸ
እስረኞቹ ድብደባ ፣ የምግብ ክልከላን ጨምሮ በተለያዩ የስቃይ ሁኔታዎች ውስጥ እንደሚያልፉ ተገልጿል
ከጦርነቱ መጀመር በኋላ 6 ሺህ ፍልስጤማውያን በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ
በአንድ ወቅት ጡንቻማ እና ጠንካራ ስፖርተኛ የነበረው ሞአዛዝ ኦባያት በእስራኤል ለ9ወራት በእስር ላይ ቆይቶ በሀምሌ ወር ከእስር ሲፈታ ያለ ሰው እርዳታ መራመድ አይችልም ነበር፡፡
ከዚያም በጥቅምት ወር ንጋት ላይ በቤቱ ውስጥ ወታደሮች ባደረጉት ድንገተኛ አሰሳ ድጋሚ ተይዞ ለወራ በእስር ቤት ይገኛል፡፡
የ37 ዓመቱ የአምስት ልጆች አባት በድጋሚ ከመታሰሩ በፊት በቤተልሔም የአዕምሮ ህክምና ሆስፒታል በከባድ “የፖስት ትራውማቲክ ዲስኦርደር” ወይም ከአደጋ ወይም ከአስቸጋሪ ጊዜ በኋላ በሚከሰት የአዕምሮ ህመም ይታከም እንደነበር ሮይተርስ ከሆስፒታሉ አገኝሁት ባለው መረጃ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ኦባያት በእስር ቤት ውስጥ "አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጥቃት እና ማሰቃየት" እንደተፈጸመበት የሚያሳይ ምልክቶች መገኘታቸውን ፣ ከቤተሰብ መራቅ እና በከባድ ጭንቀት ውስጥ እንደሚሰቃይም በህክምና መዝገቡ ላይ ተጠቅሷል፡፡
በጋዛ ጦርነት እና ከዚያ በፊት የታሰሩ በሺዎች በሚቆጠሩ እስረኞች በእስራኤል እስር ቤቶች እና ካምፖች ውስጥ ይፈፀማል የተባለው በደል እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ትኩረት እንደሚያሻው እየተነገረ ነው፡፡
ወደፊት በሚደረገው ማንኛውም የተኩስ አቁም ስምምነት እስረኞች የሚፈቱ ከሆነ ብዙዎች “ከደረሰባቸው አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጥቃት ለማገገም የረዥም ጊዜ ህክምና ይፈልጋሉ” ሲሉ የፍልስጤም እስረኞች እና የቀድሞ እስረኞች ጉዳይ ኮሚሽን ሃላፊ ቃዱራ ፋሬስ ተናግረዋል።
ሮይተርስ ይህን ዘገባ ለማዘጋጀት አነጋግሪያቸዋለሁ ያላቸው አራት ፍልስጤማውያን በድብደባ፣ በእንቅልፍ እና በምግብ እጦት እንዲሁም በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ እንዲያልፉ በመደረጋቸው ዘላቂ የስነልቦና ጠባሳ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ቢሮ በነሀሴ ወር የታተመ የምርመራ ውጤት ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በእስር ቤቶች ውስጥ ሰቆቃ፣ ጾታዊ ጥቃት እና አስገድዶ መድፈር እየተስፋፋ ስለመሆኑ የተረጋገጡ መረጃዎችን ስለማግኝቱ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።
አሜሪካ በበኩሏ በእስራኤል እስር ቤቶች በሚገኝ የእስረኞች አያያዝ ላይ የሚወጡ ተደጋጋሚ የበደል ሪፖርቶች እነዳሳሰቧት ገልጻለች፡፡
የእስራኤል ጦር በጋዛ እስረኞች ላይ እየደረሱ ነው ስለተባሉ በደሎች ማጣሪያዎችን እደረገ መሆኑን ገልጾ በታሳሪዎቹ ላይ በወታደሮች ስልታዊ በደል እየደረሰባቸው ነው የሚለውን ክስ ውድቅ አድርጓል።
ከጦርነቱ በኋላ በዌስት ባንክ እና በእስራኤል የሚገኙ ፍልስጤማውን እስረኞች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን የሚያመላክቱ ሪፖርቶች ከጋዛው ጦርነት በኋላ ብቻ ከ6 ሺህ በላይ ሰዎች መታሰራቸውን ከ50 በላይ የሚሆኑት ደግሞ መሞታቸውን ይገልጻሉ፡፡