የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት በዚህ ወር ሊፈጸም ይችላል ተባለ
የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ፤ የባይደን አስተዳደርና ትራምፕ ስምምነቱን እውን ለማድረግ በቅርበት እየሰሩ ነው ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያ ስምምነቱን ለመቀበል ትራምፕ ስልጣን እስኪይዙ እየጠበቁ ነው በሚል የሚናፈሰውን ወሬ አጣጥለዋል
በእስራኤል እና ሀማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነትን ለማስፈጸም የሚደረገው ጥረት በዚህ ወር ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ተነገረ፡፡
የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተኩስ አቁሙን በተመለከተ የሚንጸባረቁ ልዩነቶች ለስምምነት በቀረበ ሁኔታ በመጥበብ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
አማካሪው ጄክ ሱሊቫን ታጋቾችን በማስመለስ ፣ የሰብአዊ እርዳታ ስርጭትን በመጨመር እና በተኩስ አቁም የመጨረሻ ሂደት ዙርያ ለመምከር በቅርቡ በድርድር ሂደቱ እየተሳተፉ በሚገኙት ግብጽ እና ኳታር ጉብኝት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
በቀጠናው የሚገኝ የምዕራቡ አለም ዲፕሎማት ለሮይተርስ እንደተናገሩት የተኩስ አቁም ስምምነቱን የመጨረሻ ነጥቦች ለመወሰን እና ቅርጽ የማስያዝ ስራው እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡
በመጪዎቹ ሳምንታትም ከዋናው ስምምነት በፊት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ለማድረግ እና የተወሰኑ ታጋቾችን ለመልቀቅ ሁለቱ ተዋጊዎች የሚስማሙበት እድል ሊኖር ይችላል ብለዋል፡፡
ጁክ ሱሊቫን የትራምፕ አስተዳደር የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ከሆኑት ማይክ ዋልትዝ ጋር ከአንድ አመት በላይ የቆየውን ጦርነት ለማስቆም እና ቀጠናውን ለማረጋጋት በሚያግዙ ጉዳዮች ላይ እየመከሩ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት፡፡
አማካሪው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ስምምነቱን ለመቀበል ትራምፕ ስልጣን እስኪይዙ እየጠበቁ ነው በሚል የሚናፈሰውንም ወሬ አጣጥለዋል፡፡
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከበዓለ ሲመታቸው በፊት የጋዛው ጦርነት እንዲጠናቀቅ እንደሚፈልጉ እና ለዚህም ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ይታወሳል፡፡
በአዲሱ አስተዳደራቸው ውስጥ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛቸውን ወደ ስፍራው በመላክም እስራኤል እና ኳታርን ጨምሮ ከሌሎች የቀጠናው ሀገራት መሪዎች ጋር እንዲወያዩ አድርገዋል፡፡
የትራምፕ እና የባይደን አስተዳደር በጋዛው ተኩስ አቁም ስምምነት አፈጻጸም ሂደት ላይ የተለያየ መንገድ እንደሚከተሉ ቢነገርም በድርድሩ የእስራኤልን ጥቅም ለማስከበር እና የአሜሪካን የአደራዳሪነት ሚና ለማስቀጠል በጋራ ሊሰሩ እንደሚችሉ ሮይተርስ አስነብቧል፡፡
በሀማስ እጅ ይገኛሉ ተብሎ ከሚታሰቡ 100 ታጋቾችች መካከል ሰባቱ አሜሪካውያን ሲሆን ከዚህ ውስጥ አራቱ በህይወት ላይኖሩ እንደሚችሉ እየተገለጸ ነው፡፡
ሆኖም ከጥር 20 በፊት ተግባራዊ ይሆናል የተባለው የተኩስ አቁም እውን የሚሆን ከሆነ ከጥቅምት 2023 ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ሀማስ ታጋቾችችን የሚለቅ ይሆናል፡፡