እስራኤል በአልጄዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የጣለችውን እግድ አራዘመች
እስራኤል በኳታሩ የቴሌቪዥን ጣቢያ አልጀዚራ ላይ የጣለችውን እግድ በ45 ቀናት አራዘመች
የእስራኤል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኳታር በሚደገፈው አልጀዛራ ላይ የተላለፈው ውሳኔ "ማስተማሪያ የሚሆን ነው" ብሏል
እስራኤል በኳታሩ የቴሌቪዥን ጣቢያ አልጀዚራ ላይ የጣለችውን እግድ በ45 ቀናት አራዘመች
የእስራኤል ካቢኔ አልጀዚራ የሚያስተላልፈው ይዘት በእስራኤል ላይ ከባድ የደህንነት ስጋት ደቅኗል የሚል ስምምነት ላይ ከደረሰ በኋላ ተጥሎበት የነበረው እግድ በተጨማሪ 45 ቀናት ተራዝሟል።
የቴልአቪቭ ፍርድ ቤት፣ የእስራኤል መንግስት ከብሔራዊ ደህንነት ጋር በተያያዘ በጣቢያው ላይ ጥሎት የነበረውን እና ቅዳሜ የተጠናቀቀውን የ35 ቀናት እግድ ባለፈው ሳምንት አጽንቶታል።
የእስራኤል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አልጀዚራ ያቀረበውን አቤቱታ በሌላ ችሎት ተመልክቶ በኳታር በሚደገፈው አልጀዛራ ላይ የተላለፈው ውሳኔ "ማስተማሪያ የሚሆን ነው" ሲል ነው የገለጸው።
ሮይተርስ የፍርድ ቤቶቹን ሰነዶች ጠቅሶ እንደዘገበው አልጀዚራ ግጭት አለማነሳሳቱን እና እግዱ የሚያበሳጭ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።
እስራኤል በጋዛ እያደረገች ያለውን ወታደራዊ ዘመቻ የሚተቸው ጣቢያው፣ የእግዱን መራዘም በመቃወም አቤቱታ እንደሚያቀርብ ገልጿል።
የእስራኤል ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስቴር እንደገለጸው ጣቢያ በኬብሌ እና በሳተላይት በሚያደርገው ስርጭት እና በድረ ገጹ ተደራሽነት ላይ የተጣለው እግድ ይቀጥላል።
"አሸባሪው የአልጀዚራ ጣቢያ ከእስራኤል ምድር እንዲያሰራጭ እና ተዋጊዎቻችን አደጋ ላይ እንዲጥል አንፈቅድም" ብለዋል የኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ ሽሎሞ ካርሂ።
ሚኒስትሩ "በሀገሪቱ ደህንነት ላይ ያደረሰው ጉዳት ከባድ በመሆኑ እግዱ ወደፊትም እንደሚራዘም አምናሁ" ብለዋል።
ዳኛ ሻይ ያኒቭ በአልጀዚራ እና በፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ መካከል ያለውን የቆየ እና የቅርብ ግንኙነት የሚያሳይ መረጃ እንደደረሳቸው ተናግረዋል። ዳኛው አልጀዚራ የሀማስ ተልእኮ ሲያስፈጽም ነበር ሲሉ ወንጅለውታል።
አልጀዚራ በበኩሉ በሚኒስትሩ የቀረቡበትን ክሶች እና ሰበቦች ውድቅ አድርጓተዋል።
ባለፈው የፈረንጆቹ ግንቦት 5 የእስራኤል ባለስልጣናት አልጀዚራ እንደቢሮ ሲጠቀምበት የነበረውን የሆቴል ክፍል መበርበራቸው ይታወሳል።