ከሊባኖስ ወደ እስራኤል በተተኮሰ ሮኬት የአምስት ሰዎች ህይወት አለፈ
አዲሱ የሄዝቦላህ መሪ ሼክ ናይም ቃሲም የተኩስ አቁም ስምምነት እስኪደረስ ድረስ በእስራኤል ላይ የምንፈጽመው ጥቃት አይቆምም ብለዋል
እስራኤል በሊባኖስ የምትፈጽመውን የአየር ጥቃት ዛሬም አጠናክራ ቀጥላለች
ከሊባኖስ ወደ እስራኤል በተተኮሰ ሮኬት የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነገረ።
በእስራኤል ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው ሜቱላ ከተማ በደረሰው ጥቃት ህይወታቸው ካለፈው ውስጥ አራቱ የውጭ ሀገር ሰራተኞች ናቸው ተብሏል።
የከተማዋ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ ምን ያህል ሮኬቶች እንደተተኮሱ እና የሟቾቹን ዜግነት ከመግለጽ ተቆጥቧል ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።
በሊባኖስ በሶስት አቅጣጫ የተከበበችው ሜቱላ ከሊባኖስ በሚተኮሱ ሮኬቶች ከፍተኛ ጉዳት ያስተናገደች ከተማ ናት።
የከተማዋ ነዋሪዎችም ከጥቅምት 2023 ጀምሮ እንዲወጡ ተደርጎ የጸጥታ ሃይሎችና የግብርና ሰራተኞች ብቻ ቀርተው ነበር።
የውጭ ሀገር ሰራተኞችና የስደተኞች መብት ተሟጋች ተቋማትም እስራኤል የውጭ ሀገር ሰራተኞች ያለምንም የደህንነት ጥበቃ በከተማዋ እንዲቆዩ ማድረጓን ተቃውመዋል።
የዛሬው የሮኬት ጥቃት እስራኤል በሊባኖስ መጠነሰፊ ጥቃት ከጀመረች ወዲህ ከፍተኛው ሞት የተመዘገበበት ነው ተብሏል።
ጥቃቱ አሜሪካ በሊባኖስ እና በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጫና ለማድረግ አሸማጋይ ዲፕሎማቶችን በላከችበት ወቅት ነው የተፈጸመው።
በቅርቡ የሄዝቦላህ መሪ ሆነው የተሾሙት ሼክ ናይም ቃሲም በትናንትናው እለት ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት እስራኤል ተቀባይነት ያለው የተኩስ አቁም ሃሳብ እስክታቀርብ ድረስ ጦርነቱ ይቀጥላል ማለታቸው ይታወሳል።
ሄዝቦላህ ባለፉት ወራት በእስራኤል ከተፈጸመበት የመገናኛ መሳሪያዎች ፍንዳታ እና መሪዎቹ ግድያ በኋላ ዳግም ተጠናክሮ መቀጠሉንም አንስተዋል።
“የሄዝቦላህ አቅም እስካሁን አልተነካም፤ ለረጅም ጊዜ መዋጋት የሚያስችለን አቅም አለን” ሲሉም ነው የተደመጡት።
እስራኤል በበኩሏ የሄዝቦላህን ወታደራዊ ይዞታዎች መደብደቧን መቀጠሏን አስታውቃለች።
በዛሬው እለትም በደቡባዊ ሊባኖስ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች ከመኖሪያቸው እንዲለቁ አሳስባለች።
የሊባኖስ ብሄራዊ የዜና ወኪል እንደዘገበው ቴል አቪቭ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በፈጸመችው የአየር ጥቃት ስምንት ሰዎች ተገድለዋል።
እስራኤልና ሄዝቦላህ ጦርነት ከጀመሩ ወዲህ በሊባኖስ ከ2 ሺህ 800 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
ከ13 ሺህ በላይ ሊባኖሳውያንን ያቆሰለው የእስራኤል ጥቃት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ማፈናቀሉንም የሊባኖስ መንግስት አስታውቋል።
ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ በሚፈጽመው የሚሳኤል፣ ሮኬትና ድሮን ጥቃት ደግሞ 68 ሰዎች ተገድለዋል፤ ከዚህ ውስጥ ግማሹ ወታደሮች ናቸው። በጦርነቱ ምክንያት ከ60 ሺህ በላይ እስራኤላውያን ከድንበር ከተሞች ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውም ተገልጿል።