ካማላ ሀሪስ በጋዛ ያለው ጦርነት ማብቂያው አሁን ነው ማለታቸውን ተከትሎ ከእስራኤል ባለስልጣናት ትችት አጋጥሟቸዋል
የእስራኤል ባለስልጣናት ጦርነት እንዲቆም የጠየቁትን የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ተቃወሙ።
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዜደንት እና የዲሞክራት ፕሬዝደንታዊ እጩ ይሆናሉ የሚል ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ካማላ ሀሪስ በጋዛ ያለው ጦርነት ማብቂያው አሁን ነው ማለታቸውን ተከትሎ ከእስራኤል ባለስልጣናት ትችት አጋጥሟቸዋል።
ሀሪስ በአሜሪካ ጉብኝት እያደረጉ ካሉት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሜን ኔታንያሁ ስብሰባ ካደረጉ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ኔታንያሁ ከሀማስ ጋር በመስማማት ጦርነቱን እንዲያቆሙ ከተለያዩ ወገኖች ጫና እየተደረገባቸው መሆኑን አንጸባርቀዋል።
"ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴዎች አሉ፤ ግጭት ማቆሚያ ጊዜው አሁን እንደሆነ ለኔታንያሁ ነግሬዋለሁ" ብለዋል ሀሪስ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በጋዛ ሰላም ለማምጣት እና ታጋችን ለማስለቀቅ አሜሪካ ለእስራኤል ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ እንድታደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ሀማስ፣ የሀሪስን ንግግር በአሜሪካ እና በእስራኤል መካከል ክፍተት እንዳለ አድርጎ እንዳይረዳው እና ድርድሩን እንዳያርቀው ተስፋ እንዳላቸው አንድ የእስራኤል ባለስልጣን ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት እና የሪፐብሊካን እጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ጥቅምት ወር ሀማስ እስራኤል ላይ በሰነዘረው ጥቃት ምክንያት የተቀሰቀሰው ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ በማቅረብ ላይ ናቸው።
ኔታንያሁ በዛሬው እለት ከትራምፕ ጋር ይገናኛሉ ተብሏል።
የኔታንያሁ የቀኝ ዘመም ጥምረት ፓርቲ ዋነኛ ደጋፊ የሆኑት የእስራኤል የፋይናንስ ሚኒስትር ባዛሌል ስሞትሪች፣ የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ጋቪር የሀሪስን ንግግር አውግዘዋል።
"እመቤት(ካማላ ሀሪስ) ተኩስ አቁም አይኗርም" ሲሉ ቤን ጊቪር በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።
ከሀማስ ጋር ተደራድረው ግጭት እንዲቆም እና ታጋቾቸን የሚለቀቁበት ሁኔታ እንዲፈጠር በኔታኔያሁ ላይ ጫና ከሚያሳድሩት ባይደን ይልቅ የሀሪስ ንግግር ጠንከር ያለ ነው ተብሏል።
ባይደን ከምርጫ ውድድሩ ራሳቸውን ማግለላቸውን ተከትሎ የበርካታ የዲሞክሬቶችን ድጋፍ ያገኙት ሀሪስ የዲሞክራት እጩ ፕሬዝደንት ይሆናሉ የሚል ከፍተኛ ግምት አግኝተዋል።