የዩኤኢ ዜጎች እስከ 3 ወራት ለሚሆን ጊዜ ያለ ቪዛ በእስራኤል መቆየት ይችላሉ ተብሏል
የዩኤኢ ዜጎች እስከ 3 ወራት ለሚሆን ጊዜ ያለ ቪዛ በእስራኤል መቆየት ይችላሉ ተብሏል
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች(ዩኤኢ) ዜጎች ያለ ቪዛ ወደ እስራኤል እንዲገቡ የሚያስችል ስምምነት ተግባራዊ መደረጉ ተገለጸ፡፡
የዩኤኢ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር እንደገለጸው ቪዛ የማስቀረቱ ጉዳይ አቡዳቢና ቴልአቪቭ ነጻ ዝውውርን ለመፍቀድ ከተስማሟቸው ስምምነቶች መካከል ይገኝበታል፡፡
በዚህም መሰረት የዩኤኢ ዜጎች እስከ 3 ወራት ለሚሆን ጊዜ ያለ ቪዛ በእስራኤል መቆየት ይችላሉ፡፡ ይህ የመግባቢያ ስምምነት በዩኤኢ የባህል እና ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ረዳት ሚኒስትር ኦማር ቁባሽ እና በእስራኤል የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር የሕዝብና የኢሚግሬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሻሎም ሞር ዮሴፍ የተፈረመ ነው፡፡
በዚህም መሰረት የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶችን ፓስፖርት የያዙ ሰዎች ቪዛ ሳጠየቁ ወደ እስራኤል መግባት እንደሚችሉ ስምምነቱ እንደሚፈቅድ ኦማር ቁባሽ ገልጸዋል፡፡
ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት እያደገ መሆኑን እንደሚያለክት የዩኤኢ የባህል እና ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ረዳት ሚኒስትር ሚኒስትር ኦማር ቁባሽ አስታውቀዋል፡፡
የዩኤኢ እና እስራኤል በአዲሱ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸው 4 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
ይህም በቀጣናው አዲስ የትብብር አድማስን የሚከፍት እና የሕዝቦችን ብልጽግና ዕውን የሚደርግ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ኢኮኖሚያዊ አቅምን ከፍ ከማድረግ በዘለለ ቀጣይ ትውልዶችንም ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል፡፡
ዩኤኢ ከእስራኤል ጋር ይፋዊ የሆነ ግንኙነት በመመስረት ከአረቡ አለም ቀዳሚ ነች፤ ግንኙነቱም ሊመሰረት የቻለው በአሜሪካ አማካኝነት ነው፡፡