ልዑኩ ቤን ጉሪዮን አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በእስራኤሉ ጠ/ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አቀባበል ተደርጎለታል
የመጀመሪያው የዩኤኢ ልዑክ እስራኤል ገባ
የመጀመሪያው ይፋዊ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ልዑክ ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 10 ቀን 2013 ዓ.ም. እኩለ ቀን ላይ እስራኤል ደርሷል፡፡ በኤቲሃድ አየር መንገድ የተጓዙት የልዑኩ አባላት ቴል አቪቭ ቤን ጉሪዮን አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የገንዘብ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ኦባይድ ሀሚድ አል ጣይር ፣ የኢኮኖሚ ሚኒስትሩ አብዲዱላ ቢን ታውቅ አል ማሪ በዩኤኢው ልዑክ የተካተቱ ባለስልጣናት ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስቴፈን ሚኑቺን እና የዩኤኢ ባለስልጣናት የሶስትዮሽ ውይይት እዚያው በአውሮፕላን ማረፊያው በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ውይይቱ በአውሮፕላን ማረፊያው የሚደረገው በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ነው፡፡
በውይይታቸው በአቪዬሽን ፣ በኢንቨስትመንት ፣ ነፃ የመግቢያ ቪዛዎች ፣ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ መክረው ስምምነቶችን እንደሚፈራረሙ ተገልጿል፡፡
በትናንትናው እለት የመጀመሪያው የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የመንገደኞች አውሮፕላን ወደ እስራኤል ቴል አቪቭ መብረሩ ይታወቃል፡፡ ትናንት ወደ እስራኤል በረራ ያደረገው የዩኤኢ ሁለተኛው ትልቁ አየር መንገድ ኤቲሃድ ዛሬ ደግሞ የሀገሪቱን የመጀመሪያ ይፋዊ ልዑክ ይዞ በሯል፡፡